የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ በሞስኮ እያደረጉት ያለው ጉብኝት “የሰላም ጉዞ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል
የቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውን ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ሞስኮ ገብተዋል፡፡
ሺ ጂንፒንግ ሞስኮ የገቡት የሩሲያ አቻቸው በአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ በወጣባቸው ማግስት ነው።
ጉብኝቱ “ገደብ የለሽ ግንኙነት” እንዲኖራቸው ከስምምነት የደረሱት የሩሲያና ቻይና መሪዎች የሚገናኙበት እንደመሆኑ ለምእራባውን ትልቅ ራስ ምታት ነው ተብሏል፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና በቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ መካከል መደበኛ ያልሆነ ስብሰባ ይደረጋል ብለዋል፡፡
ስብሰባው በምን ላይ እንደሚያተኩር ግን ቃል አቀባዩ ያሉት ነገር የለም፡፡
የሺ ጂንፒንግ ጉብኝት በዩክሬን ምድር እየተካሄደ ያለው ደም አፋሳሽ ጦርነት በንግግር እንዲቋጭ የጀመሩት ዲፕሎማሲዊ ጥረት አንዱ አካል ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡
ጉብኝቱ “የሰላም ጉዞ” የሚል ስያሜ እንደተሰጠውም ነው ተገለጸው፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዓለም አቀፉ ወንጀሎኞች ፍርድ ቤት (አይ ሲ ሲ) የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ እጃቸውን የጨብጧቸው የሀገር መሪ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ሆነው።
አይ ሲ ሲ የእስር ማዘዣ ያወጣው በዩክሬን ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቭላድሚር ፑቲን ዋነኛው ተጠያቂ ናቸው በሚል እንደነበር አይዘነጋም፤ ምንም እንኳን ክሬምሊን ክሱን ውድቅ ቢያደርገውም፡፡
ፕሬዝዳንት ሺ ወደ ሞስኮ ከማቅናታቸው በፊት በታተመው ጽሁፋቸው ፤ የቤጂንግ ሃሳብ ዓለም አቀፋዊ አመለካከቶችን የሚያንፀባርቅ እና ሊከተሉ የሚችሉ መዘዞችን ለማስወገድ ያለመ ነው ብለዋል፡፡
"ሰነዱ የቀውሱን መዘዝ ለማስወገድ እና ፖለቲካዊ እልባት ለመስጠት እንደ ገንቢ ምክንያት ሆኖ ያገለግላል"ም ማለታቸውን ሬውተርስ በሩሲያ መንግስት በየቀኑ የሚታተመውን ሮስስካያ ጋዜጣ ጠቅሶ ዘግቧል።
ይሁን እንጅ "ውስብስብ ችግሮች ቀላል መፍትሄዎች የላቸውም " ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ቻይና 12 ነጥቦችን ያካተተ ምክረ-ሃሳብ በማቅረብ ለዩክሬን ሰላም የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ብትቀጥልበትም ፤ ዩክሬን እና አጋሮቿ የሚያቀርቡት ቅድመ ሁኔታ ሂደቱን አስቸጋሪ ሊያደርገው እንደሚችል ይገመታል፡፡
ዩክሬን እና ምዕራባውያን ደጋፊዎቿ የተኩስ አቁም ስምምነትን ለማስፈን የሚደረገውን ማንኛውንም ሙከራ ፑቲንን ለማጠናከር ጊዜ ለመግዛት ከሚደረገው ተንኮል ያለፈ ምንም ፋይዳ የለውም የሚል አቋም እንዳለቸው ይታወቃል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ሩሲያ ከዩክሬን ግዛት ሙሉ በሙሉ ካልወጣች በቀር ምንም አይነት የድርድር ጥያቄ እንደማይቀበሉ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፑቲን የዩክሬን ጦርነት እንዲያበቃ ቻይና እየተጫወተችው ለውን የሸምግልና ሚና በደስታ እንደሚቀበሉ መናገራቸውን ክሬምሊን በድረ-ገጹ አስፍሯል።
"በዩክሬን ውስጥ እየተከሰቱ ካሉት ሁነቶች ጋር በተያያዘ ቻይና ዳራዎቻቸውን እና እውነተኛ መንስኤዎቻቸውን ለመረዳት በምታደርገው ጥረት እንዲሁም በያዘቸው ሚዛናዊ አቋም ደስተኞች ነን፤ ቻይና ቀውሱን ለመፍታት ገንቢ ሚና ለመጫወት ፈቃደኛ መሆኗን በደስታ እንቀበላለን”ም ብለዋል ፑቲን፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሜሪካ እና ምዕራባውያን አጋሮቿ የቻይናን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ የሚመለከቱት ጉዳይ መሆኑ ይገለጻል፡፡
በተለይም ቤጂንግ በዩክሬን ጦርነት ሩሲያን ለማውገዝ ፍቃደኛ አለመሆኗ እንዲሁም ሌሎች ሀገራት በሞስኮ ላይ ማዕቀብ ሲጥሉ ከሞስኮ ጋር ያላትን ኢኮኖሚ ትብብር ይበልጥ እንዲጠናከር ማድረጓ ለምእራባውያን የሚዋጥ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡
አሜሪካ እና ኔቶ ቻይና ለሩሲያ የጦር መሳሪያ ለማቅረብ ታስባለች የሚል ትልቅ ስጋት እንዳለቸው ቢገልጹም፥ ቤጂንግ በተደጋጋሚ ክሱን ውድቅ አድርጋለች።