የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ አወጣ
የፍርድ ቤቱ ዳኞች በዩክሬን ለተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ፕሬዝዳንት ፑቲን ተጠያቂ ናቸው ብለዋል
ሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ጦሯ የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽመዋል የሚለውን ውንጀላ በተደጋጋሚ አጣጥላች
የአለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዳኞች በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ አወጡ።
ፍርድ ቤቱ የእስር ማዘዣ ያወጣው በዩክሬን ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የሩሲያ ፕሬዝዳንት ዋነኛው ተጠያቂ ናቸው በሚል ነው።
- የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን የምእራባውያን ዋና አላማ "ሩሲያን መበታተን ነው” አሉ
- ፑቲን ሃይፐርሶኒክ ሚሳይሎችን የጫነች መርከብ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ አሰማሩ
አንድ ዓመት ባለፈው የዩክሬን ጦርነት የሩሲያ ጦር በፕሬዝዳንት ፑቲን ትዕዛዝ በንጹሀን ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደፈጸሙ ተገልጿል።
እንዲሁም የሩሲያ ጦር በፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ ዩክሬናዊያን ህጻናትን በማገት ከእናት አባታቸው እንዲለያዩ አድርጓልም መባሉንም ሮይተርስ ዘግቧል።
ፍርድ ቤቱ ከፕሬዝዳንት ፑቲን በተጨማሪም የሩሲያ ህጻናት መብት ኮሚሽነር በሆኑት ማሪያ አሌክስያቭና ላይም ተመሳሳይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱ ተገልጿል።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንድ ዓመት ያለፈው ሲሆን ጦርነቱ ከሰው ህይወት ማለፍ ባለፈ በዓለም ምግብ፣ ዲፕሎማሲ እና ኢኮኖሚ ላይ ውስብስብ ችግሮችን አስከትሏል።
እስካሁን ከ15 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ አራት የዩክሬን ግዛቶች በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ተካለዋል።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በበኩሉ የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ትዕዛዝን ውድቅ አድርጓል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛራኮቫ እንዳሉት "የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ረብ የለሽ እና የማይተገበር ነው፣ ሩሲያ ባልፈረመችው ህግ ማንም ሊጠይቃት አይችልም" ሲሉ ለራሺያ ቱዴይ ተናግረዋል።