የቻይናው ፕሬዝዳንት ከዩክሬን አቻቸው ጋር ሊወያዩ መሆናቸውን ገለጹ
ሳውዲ አረቢያን እና ኢራንን ያስታረቀችው ቻይና ሩሲያ እና ዩክሬንንም ለማስታረቅ ጥረት ላይ ናት
ሳውዲ አረቢያን እና ኢራንን ያስታረቀችው ቻይና ሩሲያ እና ዩክሬንንም ለማስታረቅ ጥረት ላይ ናት
የቻይናው ፕሬዝዳንት ከዩክሬን አቻቸው ጋር ሊወያዩ መሆናቸውን ገለጹ።
ከቀናት በፊት ቻይናን ለሶስተኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት ዢ ጅፒንግ ከዩክሬኑ አቻቸው ጋር ሊወያዩ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ጅፒንግ ከዩክሬኑ አቻቸው ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ጋር በበይነ መረብ ታግዘው እንደሚወያዩም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጡት መግለጫ ቻይና ሩሲያን እንዳትደግፍ አሳስበው ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ከቻይና አቻቸው ጅፒንግ ጋር መወያየት እንደሚፈልጉ መግለጻቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንት ዢ ፒንግ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ሞስኮ ለይፋዊ ጉብኝት እንደሚያቀኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሞስኮ ይመክራሉ የተባለ ሲሆን የዩክሬን ጦርነት ፣ ንግድ እና ሌሎች ጉዳዮች የሁለቱ ፕሬዝዳንቶች የውይይት አጀንዳዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ቻይና በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ሩሲያን በይፋ እንድታወግዝ በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት በተደጋጋሚ መጠየቋ ይታወሳል።
ቻይና ሩሲያን አለማውገዟን ተከትሎ በተለይም የሩሲያ ነዳጅን እና ሌሎች ምርቶችን በመሸመት ሞስኮን እየደገፈች እንደሆነ ለዚህም እርምጃ እንደሚወሰድባት ዋሸንግተን አስጠንቅቃለች።