ለሁለት ቀናት ደብዘዋ ጠፍቶ የነበረችው እናት በዘንዶ ሆድ ውስጥ ተገኘች
የ45 አመቷ ኢንዶኔዢያዊት 16 ጫማ ርዝመት ካለው ዘንዶ ውስጥ አስክሬኗ ተገኝቷል
ኢንዶኔዢያ በአለም ላይ በርዝመታቸው እና በክብደታቸው ቀዳሚ የሚባሉ ዘንዶዎች መገኛ ናት
ከሀሙስ ጀምሮ የገባችበት ጠፍቶ የነበረችው ኢንዶኔዢያዊት በዘንዶ ተውጣ ህይወቷ አልፎ ተገኝታለች፡፡
ፋሪዳ የተባለችው የ4 ልጆች እናት ባሳለፍነው ሳምንት ሀሙስ ለጉዳይ ከሄደችበት ወደቤቷ ለመመለስ በምታቋረጠው ጫካ ውስጥ አዳጋው እንዳጋጠማት ተሰምቷል፡፡
ወደ ቤቷ ያልተመለሰችውን ባለቤቱን ሲያፈላልግ የቆየው ባለቤቷ አርብ አመሻሽ ላይ በዘንዶ ሆድ ውስጥ የሚስቱን አስክሬን አግኝቷል፡፡
ከሀሙስ ጀምሮ በፍለጋ ላይ የነበሩት የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለቤቷ በመንገድ ላይ ተበታትነው ያገኟቸውን የፋሪዳ እቃዎች እና የልብስ ቅዳጅ ተከትለው በጫካ ውስጥ ሲዘዋወሩ ሆዱ አብጦ የተኛ ዘንዶ ያገኛሉ፤ በሁኔታው ተጠራጥረው ዘንዶውን ከገደሉ በኋላ ሆዱን ቀደው አስክሬኑን ማውጣት ችለዋል፡፡
በሁኔታው በከፍተኛ ሀዘን ውስጥ የሚገኝው ባለቤቷ ለጉዳይ በሄደችበት አብሯት ቢጓዝ ኖሮ አደጋው ላይፈጠር ይችላል በሚል በጸጸት ውስጥ ይገኛል ሲል ፎክስ ኒውስ አስነብቧል፡፡
ኖኒ የተባለው የሟች ባለቤት "ፋፍዳ ከመሞቷ በፊት ምን አይነት ስቃይ ልታሳልፍ እንደምትችል ሳስብ እራሴን ችየ መቆም ያቅተኛል" ብሏል፡፡
በአለም ላይ ግዙፍ እና ረጃጅም ዘንዶዎች መገኛ በሆነችው ኢንዶኔዥያ መሰል ዜናዎችን መስማት እንግዳ አይደለም።
ባለፈው አመት 26 ጫማ ርዝማኔ ያለው ዘንዶ በእርሻ ላይ የሚገኝ አርሶአድር ውጦ ከቀናት በኋላ ተገኝቷል፡፡
በ2018 የ54 አመት አዛውንት ሴት በተመሳሳይ 23 ጫማ ርዝመት ባለው ዘንዶ ሆድ ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል፡፡