በኢንዶኔዥያ ምስራቅ ቲሞር በተከሰተ “ሞቃታማ አውሎ ነፋስ” የ76 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተሰማ
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ ፣ አደጋውን ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች በፍጥነት እንዲከናወኑ አዝዘዋል
አውሎ ነፋሱ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እንደቀጠለ ተገልጿል
በኢንዶኔዥያ ምስራቅ ቲሞር በተከሰተ “ሞቃታማ አውሎ ነፋስ” የሰዎችን ህይወት ማለፉ ተሰማ
በደቡብ ምስራቅ በኢንዶኔዥያ እና በምስራቅ ቲሞር በሚገኙ ደሴቶች የተከሰተውን ሞቃታማ አውሎ ነፋስ ተከትሎ ባጋጠመ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የመሬት መንሸራተት ቢያንስ የ76 ሰዎችን ህይወት ሲያልፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
በኢንዶኔዥያ ምስራቅ ኑሳ ቴንጋራ ግዛት በተከሰተው አውሎ ነፋስ እና ያንን ተከትሎ ባጋጠመ የጎርፍ መጥለቅለቅና የመሬት መንሸራተት 55 ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም 40 ሰዎች መጥፋታቸውን ነው የሀገሪቱ የአደጋ መከላከል ኤጀንሲ መረጃ የሚያመለክተው፡፡ ከ400 በላይ ሰዎች መፈናቃለቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ስጋት ላይ ሞሆናቸውም ተገልጿል፡፡
በምስራቅ ቲሞር የሚገኘውና ከኢንዶኔዥያ ጋር የሚጋራው፣ የቲሞር ደሴት ላይም በአብዛኛው በዋና ከተማዋ ዲሊ ውስጥ ባጋጠመው የመሬት መንሸራተት ፣ ጎርፍ እና የዛፎች መውደቅ ምክንያት የ21 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ ከ 1ሺህ 500 በላይ ሰዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ መደረጉንም የሲቪል ጥበቃ ዋና ዳይሬክተር ኢስማኤል ዳ ኮስታ ባቦ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
እስካሁንም በርካታ ድልድዮች መደርመሳቸውን፣ ዛፎች መውደቃቸውን፣ መንገዶች መዘጋታቸውን እና ቢያንስ አንድ መርከብ በአውሎ ነፋሱ ምክንያት በተነሳው ከፍተኛ ማዕበል ምክንያት መስመጥዋንም ነው የሀገሪቱ የአደጋ መከላከል ኤጀንሲ ያስታወቀው፡፡
ሮይተርስ የሀገሪቱን ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው ከሆነ ፣ አውሎ ነፋሱ አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየቀጠለ ነው፡፡
አደጋውን ተከትሎም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆኮ ዊዶዶ (ጆኮዊ) መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በአደጋው እጅግ ማዘናቻንና ለተጎጂ ቤተሰቦች መፅናናትን የተመኙት ፕሬዝዳንቱ “ለደረሰው አደጋ እርዳታ ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች በፍጥነት እና በጥሩ ሁኔታ እንዲከናወኑ አዝዣለሁ” ብለዋል፡፡
አውሎ ነፋሱ ከኢንዶኔዥያ አልፎ በመሄድ ላይ ቢሆንም አሁንም ቢሆን በቀጣዮቹ 24 ሰዓታት ውስጥ ይበልጥ ሊባባስ ፣ተጨማሪ ዝናብ እና ተጨማሪ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ተሰግቷል፡፡