የኢንዶኔዢያ የኔቢጤዎች የመንገድ ለይ ልመናን ወደ ቲክቶክ እያዞሩ ነው
ኢንዶኔዢያ በጎዳናዎች ላይ ልመና ብትከለክልም የበይነ መረብ ልመናው መጧጧፉ ተገለጿል
ኢንዶኔዢያውያኑ ፈጠራ በታከለበት መንገድ በቲክቶክ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል
በቲክቶክ ልመና የሰመረላቸው የኢንዶኔዢያ የኔቢጤዎች።
በደቡብ እስያዋ ኢንዶኔዢያ ጎዳናዎች ላይ ዜጎች መብዛታቸውን ተከትሎ ሀገሪቱ ልመናን ለማስወገድ ህግ ለማውጣት ተገዳለች።
ይሁንና በልመና የሚተዳደሩ የሀገሬው ዜጎች በጎዳናዎች ላይ እንዳይለምኑ ሲከለከሉ በበይነ መረብ ልመናቸውን እንደቀጠሉ ለየት ያሉ የዓለም ክስተቶችን በመዘገብ የሚታወቀው ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ በተለይም ቲክቶክ ዋነኛ የልመና ትስስር ገጽ ሆኖላቸዋል የተባለ ሲሆን እነዚህ ዜጎች ፈጠራን በመጠቀም ህይወታቸው ምን እንደሚመስል የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማሰራጨት የባለጸጎችን ትኩረት መሳባቸው ተገልጿል።
በሚያሳዩት ነገርም የገንዘብ ስጦታ ከሚሰጡ ሰዎች (ጊፍተሮች) ገቢ የሚያገኙ መሆኑ ተነግሯል።
ከ90 ሚሊዮን በላይ ኢንዶኔዢያውያን ቲክቶክን የሚጠቀሙ ሲሆን ይህም በተጠቃሚዎች ብዛት ከአሜሪካ በመቀጠል ሁለተኛዋ ሀገር አድርጓታል።
ልመናው በቲክቶክ መድራቱን ተከትሎም የሀገሪቱ መንግሥት የልመና ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዳይሰራጩ ሊያደርግ ይችላልም ተብሏል።