ኳታር ኔታንያሁ የጋዛውን ጦርነት ለማራዘም ፍላጎት አላቸው አለች
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዶሃ በሃማስ ላይ ጫና አድርጋ ታጋቾች እንዲለቀቁ ያቀረቡት ጥሪም “የሚለውጠው አንዳች ነገር የለም” ብላለች
በኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት ሲካሄድ የቆየው የተኩስ አቁም ድርድር “ተስፋ ሰጪ አይደለም” ተብሏል
የእስራኤልና ሃማስ አደራዳሪ ኳታር እስራኤል የጋዛው ጦርነት እንዲቀጥል ትፈልጋለች ስትል ወቀሰች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዶሃ በሃማስ ላይ ጫና በማድረግ እስራኤላውያን ታጋቾች እንዲለቀቁ ትርዳን የሚል ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ጥሪው “የሚለውጠው ነገር እንደማይኖር ግልጽ ነው፤ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጦርነቱን ማራዘም መፈለጋቸውን ብቻ ነው የሚያሳየው” ብለዋል የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መጂድ አል አንሳሪ።
ቃል አቀባዩ እስራኤል የታጋቾችን ጉዳይ ማጎኗን ብትቀጥልም የጦርነቱ አላማ ግልጽ እየሆነልን መጥቷል ማለታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የኔታንያሁ ዶሃ ታጋቾቹን በማስለቀቅ ሂደት ጫና ታድርግ ጥሪና ታጋቾቹ ካልተለቀቁ ተኩስ አቁም ስምምነት ላይ አንደርስም የሚለው አሰልቺ ንግግርም ጦርነቱ እንዲቆም እንደማይፈልጉ ያሳያል ነው ያሉት።
የኳታሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መሀመድ ቢን አብዱልራህማን አል ታኒ በበኩላቸው እስራኤልና ሃማስን ተኩስ አቁመው ታጋቾች እና እስረኞችን እንዲለቁ ሲካሄድ የቆየው ድርድር “ተስፋ ሰጪ አይደለም” ብለዋል።
ለአንድ ሳምንት በዘለቀ የተኩስ አቁም ስምምነት ከ100 በላይ የእስራኤል ታጋቾች እንዲለቀቁና ፍልስጤማውያን እስረኞች እንዲፈቱ ትልቅ የአደራዳሪነት ድርሻ የነበራት ዶሃ በቅርብ ቀናት ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች እየጠፉ ነው ማለቷ አሳሳቢ ሆኗል።
የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባሉ ቤኒ ጋንዝ ሁሉም እስራኤላውያን ታጋቾች ካልተለቀቁ በራፋህ የእግረኛ ጦር አስገብተን ጦርነት እንከፍታለን ማለታቸውም የኔታንያሁ አስተዳደር ጦርነቱ እንዲቀጥል መፈለጉን ያመላክታል የሚሉ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።
ከኳታር የተደመጠው ትችትም የተኩስ አቁም ንግግሮች እምብዛም ተስፋ ሰጪ እንዳልሆኑና ከ29 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ያለቁበት ጦርነት መቀጠሉ እንደማይቀር አመላካች ነው ተብሏል።
እስራኤል ለኳታር ወቀሳ ምላሽ ባትሰጥም ከዚህ ቀደም ዶሃ “ለሃማስ ድጋፍ ታደርጋለች፥ አስተያየቷም ከዚህ የተቃኘ ነው” የሚሉ አስተያየቶችን ስትሰጥ መቆየቷ ይታወሳል።