እስራኤል በራፋህ ጦርነት የምትጀምርበትን ቀን ይፋ አደረገች
ሃማስ ሁሉንም ታጋቾችን የማይለቅ ከሆነ በረመዳን ጾም መጀመሪያ የእግረኛ ጦሩ ወደ ራፋህ ይገባል ብለዋል የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባሉ ቤን ጋንዝ
ግብጽን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት በራፋህ የሚደረግ ጦርነት እጅግ ከባድ ቀውስ ያስከትላል በሚል እየተቃወሙት ነው
እስራኤል በራፋህ እግረኛ ጦሯን በማስገባት ጦርነት የምትጀምርበትን ቀን ይፋ አደረገች።
ሃማስ ሁሉንም ታጋቾችን የማይለቅ ከሆነ በረመዳን ጾም መጀመሪያ (መጋቢት 10) በራፋህ ጦርነት እንጀምራለን ብለዋል የእስራኤል የጦር ካቢኔ አባሉ ቤን ጋንዝ።
እስራኤል ወደ ራፋህ የእግረኛ ጦሯን እንደምታስገባ ስትገልጽ ይህ የመጀመሪያዋ ነው ተብሏል።
የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር “ታጋች ዜጎቻችን በረመዳን ወር መግቢያ ካልተለቀቁ ራፋህን ጨምሮ በሁሉም አካባቢ ጦርነቱ እንደሚቀጥል መላው አለምና የሃማስ መሪዎች ሊረዱት ይገባል” ነው ያሉት።
በጦርነቱ በራፋህ የሚገኙ ንጹሃን ጉዳትን ለመቀነስ ከአሜሪካ እና ግብጽ ጋር በመነጋገር ንጹሃንን ለማስወጣት ጥረት ይደረጋል ማለታቸውን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
ይህ የቤኒ ጋንዝ አስተያየት እስራኤል ፍልስጤማውያን ድንበር አቋርጠው ወደ ግብጽ እንዲገቡ ፍላጎት እንዳላት ሲነሳ የነበረውን ወቀሳ የሚያጠናክር ነው ተብሏል።
ከራፋህ ጋር የምትዋሰነው ግብጽም ከሶስት ሳምንት በኋላ የእግረኛ ጦሩ ከገባ ሊከሰት የሚችለው የፍልስጤማውያን ስደተኞች ጎርፍ ለመግታት ድንበሯን እያጠረች መሆኑን የሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎች ወጥተዋል።፡
ከፍልስጤም ህዝብ ከግማሽ በላዩ ተፈናቅሎ በሚገኝባት ራፋህ ላይ የሚከፈት ጦርነት ከባድ ቀውስ እንደሚፈጥር የሚገልጹ ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት እስራኤልን ማሳሰባቸውን ቀጥለዋል።
ይሁን እንጂ የቤንያሚን ኔታንያሁ አስተዳደር ሃማስን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስና ታጋቾችን ለማስለቀቅ የትኛውንም እርምጃ ከመውሰድ አልቆጠብም በሚለው አቋሙ እንደጸና ነው።
በኳታርና ግብጽ አደራዳሪነት በአንድ ሳምንት ከ100 በላይ ታጋቾችን ማስለቅቅ የቻለችው እስራኤል፥ አሁን ላይ ከ130 በላይ ዜጎቿ በጋዛ ታግተው ይገኛሉ፤ ከ30 በላዩም ህይወታቸው አልፏል።
የእስራኤል ጦር 136ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት በውጊያ ያስለቀቃቸው ታጋቾች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።
ጦርነቱ ከ29 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ህይወት ቀጥፎ ከ68 ሺህ በላዩን አቁስሎም ቃል የገቡት ያልሆነላቸው ኔታንያሁ ከድርድር ይልቅ አሁንም ጦርነትን የመረጡ ይመስላል።
1 ነጥብ 5 ሚሊየን ፍልስጤማውያን በተጠለሉበት ራፋህ ከአየር ጥቃቱ ባሻገር የእግረኛ ጦር አስገብተው ጦርነት ካስጀመሩም ሰብአዊ ቀውሱ በብዙ እጥፍ እንደሚጨምር ይጠበቃል።
የፍልስጤሙ ሃማስ እስከ ረመዳን መግቢያ ታጋቾችን እንዲለቅ ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።