የብራዚሉ ፕሬዝደንት የጋዛውን ጦርነት ናዚ ከፈጸመው ዘርማጥፋት ጋር ማነጻጸራቸው እስራኤልን ክፉኛ አስቆጣ
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ባለው መጠነ ሰፋ ጦርነት እስካሁን የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ29ሺ አልፏል
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሬዝዳንቱ በሰጡት አስተያየት ምክንያት የብራዚልን አምባሰደር ጠርቶ እንደሚያስጠነቅቅ አስታውቋል
የብራዚሉ ፕሬዝደንት የጋዛውን ጦርነት ናዚ ከፈጸመው ዘርማጥፋት ጋር ማነጻጸራቸው እስራኤልን ክፉኛ አስቆጣ።
የብራዚል ፕሬዝደንት ሉላ ዳ ሲልቫ እስራኤል በጋዛ በሀማስ ላይ የምታካሂደውን ጦርነት የጀርመኑ ናዚ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ከፈጸመው የዘር ማጥፋት ጋር ከነጻጸሩ በኋላ እስራኤል የዘር ጭፍጨፋውን በማቃለል እና የጀዊሽ ህዝብን በማስከፋት ከሳለች።
"በጋዛ ሰርጥ በፍልስጤማውያን ላይ እየተከሰተ ያለው ከሌሎች ታሪካዊ ሁነቶች ጋር የማይስተካከል ነው። በርግጥ እንዲህ አይነቱ ተግባር ሂትለር ጀዊሾችን ለመግደል የወሰነ ጋዜ ተከስቷል" ሲሉ ሉላ በአዲስ አበባ በተካሄደው 37ኛው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ወቅት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሬዝዳንቱ በሰጡት አስተያየት ምክንያት የብራዚልን አምባሰደር ጠርቶ እንደሚያስጠነቅቅ አስታውቋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንያሚን ኔታንያሁ የፕሬዝደንት ሉላን አስተያየት "ደስ የማይል እና ስህተት"የሆነ ሲሉ ገልጸውታል።
በብራዚል የሚገኘው የእስራኤላውያን ኮንፌደሬሽን የፕሬዝደንት ሉላ አስተያየት "እውነታውን የሚያዛባ" እና የዘር ማጥፋት ሰለባዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን ትውስታ የሚጎዳ በመሆኑ እንደሚቃወመው ገልጸዋል።
ኮንፌደሬሽኑ አክሎም የሉላ መንግስት በእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ዙሪያ "ጫፍ የወጣ እና ሚዛናዋ ያልሆነ" አቋም ይዟል ሲሉ ከሰዋል።
ፕሬዝደንት ሉላ ይህን አስተያየት ከመስጠታቸው ቀደም ብለው ለፍስጤማውያን የሰብአዊ እርዳታ ለሚያደርሰው የተመድ ኤጀንሲ ድጋፍ መቋረጡን አውግዘው ነበር።
ፕሬዝደንቱ " ጦርነቱ በወታደሮች እና በወታደሮች መካከል የሚደረግ አይደለም፤ ከፍተኛ ዝግጅት ባደረገ ወታደር እና በሴቶች እና በህጻናት መካከል እየተደረገ ያለ ጦርነት"ብለዋል።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ባለው መጠነ ሰፋ ጦርነት እስካሁን የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ29ሺ አልፏል።