ኳታር ለጋዛ የምታደርገው ድጋፍ፤ የእስራኤል ይሁንታና ፍላጎት፤ የዋሽንግተን ሚና
ዶሃ ከ2018 ጀምሮ በየወሩ ሚሊየን ዶላሮችን ለጋዛ ለመስጠት ስትወስን ከእስራኤል ጋር ስምምነት ደርሳለች
እስራኤልና ሃማስን የሰባት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደርሱ ያደራደረችው ኳታር የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ መቀመጫ ናት
ሃማስ በጥቅምት 7 2023 በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ካደረሰ በኋላ የእስራኤልና አሜሪካ ፖለቲከኞች ጣታቸውን ኳታር ላይ ሲሰነዝሩ እንደነበር ይታወሳል።
ዶሃ ሚሊየን ዶላሮችን በሃማስ ለምትተዳደረው ጋዛ የማቅረቧ ጉዳይ ለቴል አቪቭም ሆነ ዋሽንግተን የተደበቀ ነገር ግን አልነበረም።
እንደውም የእስራኤል ይሁንታ የነበረበት ጉዳይ ነበር።
ሲኤንኤን በእስራኤል የምርመራ ጋዜጠኛነት ስራን ከሚከውነው ተቋም ሾምሪም ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትልም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጭምር በጉዳዩ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው አረጋግጧል።
ኳታር ለጋዛ የገንዘብ ድጋፍ መቼ ጀመረች?
ኳታር በጋዛ ለወርሃዊ ደመወዝ የሚውል ክፍያ መላክ የጀመረው በፈረንጆቹ 2018 ነው።
የዌስትባንክን የሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር (ፒኤ) በ2017 ሃማስ ለሚያስተዳድራት ጋዛ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ አልከፍልም ማለቱን ተከትሎ ነው ዶሃ ድጋፉን የጀመረችው።
ኳታራውያን 15 ሚሊየን ዶላር የያዘ ቦርሳን የእስራኤልን ድንበር አቋርጠው ወደ ጋዛ ይዘው እንዲገቡም ለወራት የወሰደ ድርድር ተካሂዷል።
ሙሀሙድ አባስ የሚመሩት የፍልስጤም አስተዳደር የኳታርን ውሳኔ ቢቃወሙም እስራኤል ለዶሃ ፍቃድ በመስጠቷ ለአመታት ድጋፉ መቀጠሉን ነው ሲኤንኤን የዘገበው።
ሃማስ በበኩሉ የገንዘብ ድጋፉ ለመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ እና ለመድሃኒት ግዥ የሚውል መሆኑን በመጥቀስ የፍልስጤም አስተዳደር የሚያነሳውን አስተያየት ሲያጣጥል ቆይቷል።
ሃማስ ከሁለት ወራት በፊት በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲፈጽም ቴል አቪቭ ጣቷን ዶሃ ላይ ብትቀስርም ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በነሃሴ ወር 2018 ለደህንነት ካቢኔያቸው አቅርበው ማጸደቃቸውንም ዘገባው ያወሳል።
ኔታንያሁ በወቅቱ ከተቃዋሚዎቻቸው ለቀረበባቸው ወቀሳም ስምምነቱ (ከዶሃ ጋር የተደረሰው) በጋዛ ሰብአዊ ቀውስ እንዳይከሰት ይረዳል በሚል አጣጥለውት ነበር።
አሜሪካም ኳታር ወርሃዊ ድጋፉን እንድታደርግ በማመቻቸቱ ሂደት ተሳታፊ እንደነበረች ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቀድሞው የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ነግረውኛል ብሏል ሲኤንኤን።
እስራኤል የዶሃን የገንዘብ ድጋፍ ለምን ፈለገችው?
የእስራኤልና አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ኔታንያሁ በኳታር በኩል ለጋዛ ወርሃዊ ድጋፉ እንዲቀርብ የፈለጉት ሃማስ የፍልስጤም አስተዳደር ተቀናቃኝ ሆኖ እንዲወጣና የፍልስጤም ነጻ ሀገር የመመስረት ጉዞን ለማሰናከል ነበር የሚሉ ዘገባዎችን አውጥተው ነበር።
የፍልስጤም አስተዳደር (ፒኤ)ም የዶሃ ድጋፍ የፍልስጤም ተፋላሚ ሃይሎች ክፍፍል ይበልጥ እንዲሰፋ ማድረጉን መግለጻቸውንም በማከል።
በእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን የነበሩት ሜጀር ጄኔራል አሞስ ጊላድ፥ በኔታንያሁ ይሁንታ የተሰጠው ጉዳይ በሚስጢር መያዙንና “ሃማስን በቂ ገንዘብ ካቀረብንለት የነጻናት ትግሉን ይተወዋል” የሚል የተዛባ አመለካከት እንደነበር ያወሳሉ።
የእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ምክትል የነበሩት ሽሎሞ ብሮም ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የፍልስጤማውያን ተፋላሚ ሃይሎች መከፋፈል ኔታንያሁ ከየትኛው ጋር የሰላም ንግግር ላድረግ የሚል መከራከሪያ እንዲያነሱ አግዟቸዋል ብለዋል።
እስራኤል ሃማስ እና የሙሀመድ አባሱን የፍልስጤም አስተዳደር እያጋጨች የፍልስጤማውያንን ነጻ ሀገር የመመስረት ትግል ለማኮሰስ የዶሃን የገንዘብ ድጋፍ ፈቅዳለች ነው የተባለው።
የኔታንያሁ አስተዳደር ግን ይህን ወቀሳ አይቀበለውም፤ ኳታር ድጋፍ እንድታደርግ የፈቀድነው በጋዛ ሰብአዊ ቀውስ እንዳይከሰት በማሰብ ነው ይላል።
ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ መቀመጫዋ ዶሃ ወደ ጋዛ የምትልከው ገንዘብ ለተፈለገው አላማ ውሏል ወይስ ሃማስ ወታደራዊ ሃይሉን አጠናክሮበታል የሚለው ግን አጠያያቂ ነው።
ኔታንያሁ እና አጋራቸው አሜሪካ ከጥቅምት 7ቱ ጥቃት በኋላ ዶሃን የመውቀስ ሞራል አላቸው ወይ የሚሉ እስራኤላውያንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃማስ አቅሙ እንዲፈረጥም ተባባሪ ናቸው በሚል ቤታቸው ድረስ በመዝለቅ ሲቃወሟቸው ታይቷል።
ከእስራኤል፣ ከአሜሪካ እና ከፍልስጤሙ ሃማስ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ዶሃ በበኩሏ ለፍልስጤማውያን የማቀርበውን ድጋፍ አላቋርጥም በሚለው አቋሟ ጸንታለች።