ኳታር ወደ አውሮፓ የምትልከውን ነዳጅ ልታቆም እንደምትችል አስጠነቀቀች
ሀገሪቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰችው የአውሮፓ ህብረት የሰብዓዊ እና አካባቢ ጥበቃ ህግ ማውጣቱን ተከትሎ ነው
የኢትዮጵያ ቡና ንግድ በአውሮፓ አዲስ ህግ ምክንያት እክል ሊገጥመው ይችላል መባሉ ይታወሳል
ኳታር ወደ አውሮፓ የምትልከውን ነዳጅ ልታቆም እንደምትችል አስጠነቀቀች፡፡
የመካከለኛ ምስራቋ ኳታር ወደ አውሮፓ ነዳጅ ከሚልኩ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡ የአውሮፓ ህብረት ከወራት በፊት ከሰብዓዊ መብት እና አካባቢ ጥበቃ ጋር የተያያዘ አዲስ ህግ አውጥቷል፡፡
ይህ ህግ በተለይም የሰራተኞች መብት የማያከብሩ እና የአካባቢ ጥበቃን ባልጠበቀ መንገድ የተመረቱ ምርቶች ወደ አውሮፓ እንዳይገቡ የሚከለክል ነው፡፡
በነዳጅ ሀብቷ የምትታወቀው ኳታር ይህ ህግ ከተተገበረ ወደ አውሮፓ የምትለከውን ነዳጅ ልታቆም እንደምትችል አስጠንቅቃለች፡፡
የሀገሪቱ ኢነርጂ ሚኒስትር ሳአድ አል ካቢ ለፋይናንሺያል ታየምስ እንዳሉት አውሮፓ ህብረት በዚህን ህግ ምክንያት ወደ ቅጣት ከገባ ነዳጅ መላካችንን እናቆማለን ብለዋል፡፡
በዚህ ህግ መሰረት የአውሮፓ ህብረት የሰራተኞችን መብት ጥሰው በተመረቱ እና ወደ አህጉሪቱ የሚገቡ ምርቶች ተገቢውን ህግ አክብረው መመረታቸውን ማረጋገጥ አለባቸውም ይላል፡፡
ሀገራት አልያም ተቋማት ይህን ህግ እንዳልጣሱ ካላረጋገጡ በአውሮፓ ገበያ ከሸጡት ምርት ውስጥ የ5 በመቶውን እንደሚቀጡም ይደነግጋል፡፡
የኳታር ሀይል ሚኒስትር ህብረቱ በአውሮፓ ከሸጥነው ነዳጅ ውስጥ 5 በመቶውን የሚቀጣን ከሆነ ከነጭራሹ ነዳጅ ላለመላክ እንገደዳለን ሲሉም ተናግረዋል ተብሏል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ያወጣው ይህ ህግ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራትን ሊጎዳ ይችላል የተባለ ሲሆን በተለይም የኢትዮጵያ ቡና እና አበባ ምርቶች ዋነኛ ተጎጂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
አዲሱ የአውሮፓ ህብረት አካባቢ ጥበቃ ሕግ የኢትዮጵያን ቡና ገበያ ምን ያህል ይጎዳል?
ኢትዮጵያ ከጠቅላላው የወጪ ንግድ ውስጥ 30 በመቶውን ወደ አውሮፓ የምትልክ ሲሆን በዚህ ህግ ምክንያት የገበያ ድርሻዋን ላለማጣት ከህብረቱ ጋር በጋራ እየሰራች መሆኗን በተደጋጋሚ አሳውቃለች፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር አዲሱ የአውሮፓ ህብረት ህግ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የቡና ገበሬዎችን እንደሚጎዳ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና አመራረት ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የሚቃረን አይደለም የሚለው ማህበሩ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ እንዲረዳ ከመንግስት ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሆነም የማህበሩ ፕሬዝዳንት ከወራት በፊት በጉዳዩ ዙሪያ ከአል ዐይን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ላይ ተናግረው ነበር፡፡