“ለዩክሬን ጦርነት የተሰጠው 300 ቢሊየን ዶላር በአውሮፓ ተዓምር ይሰራ ነበር” - ቪክቶር ኦርባን
የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ምዕራባውያን ለዩክሬን ጦርነት የለገሱት ገንዘብ የአህጉሩን በርካታ ችግሮች ይፈታ ነበር ብለዋል
ለጦርነት የዋለው ገንዘብ እና ሀይል ሰላማዊ አማራጮችን ለማፈላለግ መዋሉ ላይ እጠራጠራለሁ ሲሉ ተናግረዋል
በ2022 የዩክሬን ጦርነት ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ አሜሪካ ምዕራባውያን የ310 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ እና ወታደራዊ ድጋፍ ማድረጋቸውን የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶረ ኦርባን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትላንትናው እለት ከኮሱት ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደዚህ ያለ ከፍተኛ ገንዘብ በአውሮፓ ህብረት ውስጥ የሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል ቢውል “አስደናቂ ነገር ሊሠራ ይችል ነበር” ብለዋል፡፡
ኦርባን በጦርነት ላይ የዋለው በመቶ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ የአውሮፓ መሠረተ ልማትን ለማጠናከር፣ የምዕራብ ባልካን ሀገሮችን በአውሮፓ ህብረት ደረጃ ልክ ለማልማት ወይም ወታደራዊ አቅምን ለማጎልበት ጥቅም ላይ ሊውል ይገባ ነበር ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
በቃለ መጠይቁ እየተሻሻለ የመጣው ወታደራዊ ሁኔታ ወደ ሩሲያ እያዘነበለ ነው ያሉት ኦርባን፤ ዶናልድ ትራምፕ በሚቀጥለው ወር ወደ ኋይት ሀውስ መመለስ በአሜሪካ የሚያስከትለውን የፖለቲካ እና የፖሊሲ ለውጥ ጠቁመዋል።
ወቅታዊ ሁኔታዎች የህብረቱ መሪዎች በአህጉሩ ውስጥ ደህንነትን እና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የበለጠ ተቀራርበው እንዲሰሩ የሚጠይቁ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያምናሉ፡፡
ነገር ግን ህብረቱ ቅድሚያ በሚያስፈልጋቸው ሁኔታዎች ላይ ለማተኮር ፈቃደኛ አይደለም፤ በቅርቡ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ለኪየቭ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ያሳለፈው ውሳኔም ይህን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ለጦርነት የዋለው ሀይል እና ገንዘብ ድርድርን ለማስፈጸም እና ሰላማዊ አማራጮችን ለመፈለግ መዋሉ ላይ እጠራጠራለሁ ነው ያሉት፡፡
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ኦርባን በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል የገና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ለመጨረሻ ጊዜ ተቀባይነት ያላገኝ ሀሳብ አቅርበው ነበር፡፡
ዩክሬንን መደገፍ ጦርነቱን ማራዘም ነው የምትለው ሩሲያ ምንም ያህል መጠን ያለው የምዕራባውያን ዕርዳታ ጦሯን የወታደራዊ ዘመቻውን ዓላማ ከማሳካት እንደማያግደው ወይም የግጭቱን የመጨረሻ ውጤት እንደማይለውጥ ደጋግማ አስጠንቅቃለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ምዕራባውያን የኔቶ አባላት በዩክሬን እና ሩሲያ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት የሚፈጸም ከሆነ የሰላም አስከባሪ ጦር እንዲሰማራ ጠይቀዋል፡፡
ሀገራቱ ስምምነቱ ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ ሞስኮ ዳግም በዩክሬን ላይ ጦርነት ላለማወጇ እና የስምምነቱን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ ከሀገራት የተውጣጣ ጦር በዩክሬን እንዲሰማራ ጠይቀዋል፡፡