ኳታር ለዓለም ዋንጫ ያዘጋጀቻው ስታዲየሞች ምን ይመስላሉ?
ዶሃ ትናንትና ከዛሬ ያዋሃዱ ባህልና ታሪኳን በድንቅ ኪነህንፃ ጥበብ ያንፀባረቁ ስታዲየሞችን ገንብታለች
በድንኳን ቅርፅ ከተሰራው አል ባይት አንስቶ በ974 ኮንቴነሮች እስከተገነባው ስታዲየም ኳታር ቢሊየን ዶላሮችን አፍስሳባቸዋለች
የ2022 የአለም ዋንጫ የመጀመሪያ የሚያሰኙት በርካታ ነገሮች አሉ።
በመካከለኛው ምስራቅ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተካሄደ ያለው የኳታሩ የአለም ዋንጫ፥ በአንድ ቀን ከአንድ በላይ ጨዋታዎችን መመልከት የሚያስችል መሆኑም ፈር ቀዳጅ ያደርገዋል።
ሁሉም ስታዲየሞች፣ የመለማመጃና የመዝናኛ ስፍራዎቹም በፀሃይ ሃይል የሚሰሩ ማቀዝቀዣዎች የተገጠሙላቸው ናቸው።
በህዳር ወር እየተካሄደ ያለው የአለም ዋንጫ በሙቀት እንዳይረበሽም ኳታር ሙቀታቸውን በሪሞት የምታስተካክላቸውን ስታዲየሞች ለአለም በይፋ እያስተዋወቀች ነው።
ኳታር ለአለም ዋንጫው ማስተናገጃ የገነባቻቸው ስታዲየሞች የዘመኑን ቴክኖሎጂ ከማሟላት ባለፈ የሀገሪቱ ባህልና እሳቤም የተንፀባረቀባቸው ናቸው።
የስምንቱንም ስታዲየሞች ገፅታ በተወሰነ መልኩ እንመልከት፦
1. አል ባይት ስታዲየም
በግዙፍ ድንኳን ቅርፅ የተሰራው የአል ባይት ስታዲየም፥ 60 ሺህ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚያስችሉ መቀመጫዎች አሉት። ስታዲየሙ ባይት አለሰ ሻር ከሚሰኙ በኳታርና በባህረ ሰላጤው ሀገራት ኑሯቸውን በአርብቶ አደርነት ካደረጉ ጎሳዎች ስያሜውን አግኝቷል።
የኳታርን ትናንት እና ዛሬ የሚያመላክት ዲዛይን ያለው የአል ባይት ስታዲየም፥ የአረንጓዴ ልማት ሞዴል ተደርጎም ይወሰዳል። አል ባይት ከአለም ዋንጫው በኋላ መቀመጫዎቹ ወደ 32 ሺህ ዝቅ ይደረጋሉ።
2. አህመድ ቢን አሊ ስታዲየም
በማዕከላዊ ዶሃ የሚገኘው የአህመድ ቢን አሊ ስታዲየም፥ የኳታር አየር ንብረትን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ተብሎለታል። የስታዲየሙ ጣሪያ የአሽዋ ክምር ይመስላል፤ በዙሪያው የሚታየው ሁሉ የኳታርን የበርሃ ገነትነት ያንፀባርቃል ነው የተባለለት። ይህ ስታዲየም 40 ሺህ ተመልካቾችን በመቀመጫ ማስተናገድ ይችላል።
3. አል ጃኖብ ስታዲየም
የአል ዋክራህ ከተማ ነዋሪዎች በአሳ ንግድ ይተዳደሩ እንደነበር መረጃዎች ያወሳሉ። ኳታርም በዚችው ከተማ ስታዲየም ስትገነባ ዲዛይኑን ማዕበል የሚያናውጠው ጀልባ አድርጋዋለች። በአል ዋክራህ ከተማ በስተደቡብ የሚገኘው የአል ጃኖብ ስታዲየም፥ 40 ሺህ ተመልካቾችን የማስተናገድ አቅም አለው።
4. ካሊፋ አለም አቀፍ ስታዲየም
የካሊፋ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በፈረንጆቹ 1976 ነው የተሰራው። ኳታር የ2006ቱን የእስያ የእስያ ጨዋታዎች ስታስተናግድ የታደሰው ይህ ስታዲየም ለዘንድሮው ዋንጫም ተሰናድቷል። 40 ሺህ ተመልካች መያዝ የሚችለው የካሊፋ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በውስጡ ያካተታቸው የስፓርት ስፍራዎች፣ ሆስፒታልና ሙዚየምም ልዩ ድምቀት ሆነውታል።
5. ኢጁኬሽን ሲቲ ስታዲየም
ኳታር በአለም አቀፍ ደረጃ አንቱታን ያተረፉ ዩኒቨርሲቲዎች የተሰባሰቡበት ግዙፍ መንደር አላት። በዚሁ አካባቢ የተገነባው ስታዲየምም በዘመናዊነቱ ተጠቅሷል። 40 ሺህ ተመልካች መያዝ የሚችለው ስታዲየሙ ከአለም ዋንጫው በኋላ ከግማሽ በላይ መቀመጫዎቹ ይነቀላሉ ተብሏል።
6. ሉሳይል ስታዲየም
ኳታር የ2022ቱ የአለም ዋንጫ ያስገነባችው ሉሳይል ስታዲየም የፍፃሜ ፍልሚያውን ያስተናግዳል።
80 ሺህ ተመልካቾችን እንዲያስተናግድ ተደርጎ የተገነባው ስታዲየሙ፥ ከአለም ዋንጫው በኋላ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ካፍቴሪያዎች እና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ወደሚያካትት ማዕከልነት ይለወጣል።
7. 974 ስታዲየም
የ974 ስታዲየም ፕሮጀክት ከአለማችን የስፓርት ስታዲየም ግንባታ ፈር ቀዳጅ መሆኑ ተነግሯል። ከ974 ኮንቴነሮች የተሰራው ስታዲየም አለም ዋንጫው ሲጠናቀቅ ሙሉ በሙሉ ፈርሶ ለግንባታ የዋሉት ቁሳቁሶችም ዳግም ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይደረጋል መባሉ አግራሞትን አጭሯል። 974 የኳታር የስልክ መነሻ ኮድ መሆኑንም ልብ ይሏል። ከግዙፉ ሃማድ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ የተገነባው የ974 ስታዲየም በባህር ዳርቻ አቅራቢያ መገንባቱም ልዩ ድምቀት ሰጥቶታል።
8. አል ቱማማ ስታዲየም
የአረቦች የኪነህንፃ ብቃት የታየበት የአል ታሙማ ስታዲየም ሙስሊሞች በሚያደርጉት ቃህፊያ የተሰኘ ኮፍያ ቅርፅ ነው የተገነባው። የአረብ ሀገራት ባህላዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖናታዊ ትስስር የተነንፀባረቀበት ስታዲየም 40 ሺህ ተመልካቾችን ያስተናግዳል።
ኳታር ከገነባቻቸው ስምንት ስታዲየሞች 170 ሺህ መቀመጫዎችን በመንቀል ለታዳጊ ሀገራት ለመለገስ ቃል መግባቷ ይታወሳል።
ዶሃ ከአለም ዋንጫው በኋላ የሚኖሯት ስታዲየሞች የመቀመጫ ብዛት ከ25 ሺህ እንደማይበልጥም ተነግሯል።