በዓለም ዋንጫ የነገሰችው ብራዚል 6ኛ ዋንጫዋን ታነሳ ይሆን?
በሁሉም የአለም ዋንጫዎች የተሳተፈችው የላቲን አሜሪካዋ ሀገር ከ2002 ወዲህ ዋንጫውን አላነሳችም
በኔይማር የሚመራው የብራዚል የፊት መስመር የ20 ዓመት ያለዋንጫ ጉዞዋን እንደሚገታ ይጠበቃል
ባለፉት አራት የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች በአውሮፓ ሀገራት ከዋንጫ ፉክክር የተሰናበተችው ብራዚል፥ በኔይማር የሚመራው አስፈሪ የፊት መስመሯ የ20 አመት ያለዋንጫ ጉዞዋን እንደሚገታ ይጠበቃል።
በኡራጓይ በ1930 በተጀመረው የአለም ዋንጫ ያለማቋረጥ የተሳተፈችው የላቲን አሜሪካዋ ብራዚል ናት።
አምስት ጊዜ ዋንጫውን በማንሳትም የሚስተካከላት የለም። በ21ዱ የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች 73 ጊዜ ድል አስመዝግበዋል፤ በ18ቱ አቻ ሲወጡ 18 ጊዜ ደግሞ ሽንፈትን አስተናግደዋል።
ቢጫ ለባሾቹ ሴሌሳዎች ከፔሌ እስከ ሮናልዶ የአለም ዋንጫው ድምቀት የሆኑ ከዋክብት ስብስብ ነው።
ቲቴ በሚለው ቅፅል ስማቸው የሚታወቁት አሰልጣኝ አዴኖር ሊዮናርዶ ባቺ ሀገራቸውን ከ20 አመት በኋላ ሻምፒዬን ለማድረግ ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።
በሮቤርቶ ማርቲኔዝ የምትሰለጥነው ቤልጂየም ከሩስያው የአለም ዋንጫ ከሩብ ፍፃሜ ውጭ የሆኑት ቲቴ የአውሮፓ ሀገራትን መቋቋም ተስኗቸዋል።
ባለፉት አራት የአለም ዋንጫዎች በዜነዲን ዚዳኗ ፈረንሳይ፣ በአሪያን ሮበኗ ሆላንድ፣ በቶኒ ክሮሷ ጀርመን እና ኬቨን ደ ብሩይኗ ቤልጂየም ነው ብራዚል ከውድድር ውጭ የሆነችው።
በኳታሩ የአለም ዋንጫም ከሰርቢያ እና ስዊዘርላንድ ጋር በአንድ ምድብ ተደልድድላለች። ሀገራቱ ዝቅ ያለ ግምት ቢሰጣቸውም ኮረንቲያስን ጨምሮ በርካታ ክለቦችን ያሰለጠኑት የ61 አመቱ ቲቴ የረጅም እድሜ ልምዳቸው አስተምሯቸዋል።
የፔሌን የብራዚል የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪነት ሪከርድ ሊሰብር ሶስት ጎሎች የቀሩት ኔይማር የሚመራው የፊት መስመርም ምኞታቸውን እንዲያሳካላቸው ይጠብቃሉ።
በኳታር ሶስተኛ የአለም ዋንጫ ተሳትፎውን የሚያደርገው ኔይማር በአለም ዋንጫው ስድስት ጎሎችን አስቆጥሯል።
በ121 አለም አቀፍ ጨዋታዎች 75 ጎሎችን ለሀገሩ በማስቆጠር ከፔሌ ቀጥሎ ያስቀመጠውን ውጤት ለማሻሻልም የኳታሩ የአለም ዋንጫ ትልቅ እድል ይዞለት መጥቷል።
በርካቶች ግን ኔይማር በተጠበቀው አይገኝም ይሉታል።
የቲቴ በወጣት የተገነባውና ከአምስት በላይ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች የያዘው ቡድን እንደ ቲያጎ ሲልቫ ባሉ ልምድ ያላቸው ተከላካዬች ተገንብቷል።
ብራዚል ፔሌ ሲጎዳ እንደተካው ጋሪንቻ የቁርጥ ቀን ልጅ ግን አሁን ላይ ያላት አይመስልም። ሮናልዶ በኋላም ሁነኛ 9 ቁጥር ተጫዋች አጥታለች።
ከ20 አመት በፊት ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ባዘጋጁት የአለም ዋንጫ ጀርመንን አሸንፈው ዋንጫ ሲያነሱ ሮናልዶ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነበር።
ባለፉት ሁለት የአለም ዋንጫ ፍሬድም ሆነ ጋብሬል ጄሰስ የተጠበቁትን አልሆኑም። በኳታር ግን በ38 ጨዋታዎች ለብራዚል 17 ጎሎችን ያስቆጠረው ሪቻልሰን ይጠበቃል።
ሴሌሳዎቹ በምድብ 7 ከስዊዘርላንድ፣ ሰርቢያ እና ካሜሮን ጋር ተደልድላለች።