በምርጫው ላይ የሚነሱ የተገቢነት ጥያቄዎች “ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዳይኖረን የሚያደርጉ ናቸው”- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ
ሁሉም የምርጫ ካርድ እንዲያወጣም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል
ፓርላማው “የእውነተኛ ፓርላማነት ባህሪን” ባለመላበሱ ምክንያት ሕዝባዊ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ለመመለስ ሳይቻል መቅረቱን ገልጸዋል
ምርጫውን በዚህ ሰዓት ማድረግ ቅንጦት ነው በሚል የሚቀርቡ የተገቢነት ጥያቄዎች “ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዳይኖረን የሚያደርጉ” ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብን ጥያቄዎች “ከጎዳና ወደ ፓርላማ” የሚወስድ ነው በሚል ምርጫውን የተመለከተ መግለጫ አውጥተዋል፡፡
በመግለጫው በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት የሕዝቦችን ጥያቄ ወደ ተገቢው የዴሞክራሲ ባሕል መንገድ ማስገባት ሳይቻል እንደቀረ ያነሱ ሲሆን “የዘንድሮው ምርጫ የዘመናት ቋጠሮዎች የሚፈቱበት ቁልፍ እንደሆነ መዘንጋት ሞኝነት ነው” ብለዋል፡፡
ሕዝባዊ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ለመመለስ “አንድም በጎዳና ላይ ዐመጽ፣ ሁለትም በጦር መሣሪያ አማካኝነት” በተደረጉ ጥረቶች ብዙ ውድመት ማጋጠሙንም ነው በመግለጫቸው ያስቀመጡት፡፡
ለዚህ ምክንያቱ “የሕዝብ ድምፆች ተገቢውን ቦታ አግኝተው መሰማት አለመቻላቸው ነው”ም ብለዋል የሃገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) “የእውነተኛ ፓርላማነት ባህሪን” ለመላበስ አለመቻሉን በማሳያነት በመጠቆም።
የዘንድሮው ምርጫ “ወርቃማ” ያሉትን ይሄን እድል ለኢትዮጵያውያን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ከክልል አመራሮች እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ቀሪ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ እና ያልተጠናቀቁ ጉዳዮች እንዲጠናቀቁ አቅጣጫ ማስቀመጣቸው ይታወሳል።
የምርጫው ሂደት ላይ የተአማኒነት ጥያቄ ሊያስነሱ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ቀደም ብሎ ርምጃዎች መወሰዳቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም የሚፈቅደውን ተፎካካሪ የሚመርጥበትን ካርድ እንዲያወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ‘ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው እየተገደሉና እየተፈናቀሉ፣ ሽምቅ ተዋጊዎች ሰላማዊውን ሕዝብ ረፍት ነስተው ባሉበት በዚህ ወቅት ስለ ምርጫ መጨነቅ ተገቢ አይደለም፤ ተጨማሪ ቀውሶችን ሊጋብዝም ይችላል’ በሚል ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በምላሻቸው ጥያቄዎቹ “አሳማኝና የሰዎችን ልብ የሚገዙ ቢመስሉም” ሲፈተሹ “ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚወድቁ ናቸው” ነው ያሉት፡፡
ጥያቄዎቹ “የሕዝብ ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዳይኖረን የሚያደርጉ ናቸው”ም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከደካማ መንግስት ምንም እንደማታተርፍም ገልጸዋል፡፡
ምርጫው የሕዝቦችን ጥያቄ ከጎዳና ወደ ፓርላማ ከማስገባት በተጨማሪ ለሃገር የሚጠቅም ቅቡልነት ያለው መንግሥት ለመመሥረት እንደሚያስችልም ነው በመግለጫቸው ያስቀመጡት፡፡
6ተኛውን አገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ/ም ለማካሄድ ዝግጅቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
የመራጮች ምዝገባ እስከ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 መራዘሙ የሚታወስ ነው፡፡
እስከ ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ 18 ሚልዮን 427 ሺህ 239 ዜጎች (18,427,239) በመራጭነት መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡