በጸጥታ ችግር የተነሳ በ 4,126 የምርጫ ጣቢያዎች የቁሳቁስ ስርጭት እና የመራጮች ምዝገባ መዘግየቱን ቦርዱ ገለፀ
ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ክፍተት ያለባቸው ጣቢያዎች የሚገኙባቸው ክልሎች ኦሮሚያ ፣ አማራ ፣ ደቡብ እና ቤኒሻንጉል ናቸው
ተፈናቃዮች በሚኖሩበት የልዩ ምርጫ ጣቢያዎችን ለማደራጀት ቢዘጋጅም ችግሮች መኖራቸውን ቦርዱ አስታውቋል
የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን መረጃዎች መሰረት አድርጎ ለተፈናቃዮች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን ለማደራጀት አጠቃላይ ዝግጅት መደረጉን የምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ይሁን እንጂ በተፈናቃይ ጣቢያዎች እና ሌሎች ቦታዎች ምርጫ ጣቢያ ለማደራጀት ያጋጠሙ ችግሮች መኖራቸውንም ያሳወቀው ቦርዱ ፣ ከነዚህም አንደኛውየአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የከልል ኮሚሽነሮች በክልላቸው ያለውን የተፈናቃይ ቁጥር፣ እና ተያያዥ መረጃዎች በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ አብዛኛው የተሟላ ምላሽ አለመስጠታቸው መሆኑን አንስቷል፡፡ የተሟላ ምለሽ ያቀረበው የደ/ብ/ብ/ህ ክልል ኮሚሽን ብቻ እንደሆነም ነው የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ብርትኳን ሚደቅሳ የገለጹት።
የተፈናቃዮችን ቁጥር፣ የካምፓችን ብዛት፣ የካምፓችን ልዩ ተጠሪ…ወዘተ በተመለከተ አንዳንድ ክልሎች የቃል ምላሽ የሰጡ ሲሆን በጽሁፍ አስፈላጊ መረጃዎች ያሟላ ክልል እንደሌለም ወ/ሮ ብርትኳን ገልጸዋል፡፡
የመራጮች ምዝገባ እና ጸጥታ
በፀጥታ ስጋት እና የመረጃ መዘግየት የተነሳ የመራጮች የምዝገባ ቁሳቁሶች ስርጭት በአንዳንድ አካባቢዎቻቸው የዘገየባቸው ክልሎች አሉ፡፡ እነዚህም፡
1. ኦሮሚያ ክልል - ምእራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮጉድሩ እና ቄለም ወለጋ (ከልሉ
ስለቀበሌዎቹ ፀጥታ የሰጠው መረጃ ዘግይቶ የደረሰ በመሆኑ እና መረጃዎቹም ከደረሱ በኋላ
መጣራት ስለነበረባቸው የዘገየ)
2. ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ከልል - መተከል ዞን እና ከማሺ ዞን (በከፊል)
3. አማራ ክልል - ኦሮሚያ ልዩ ዞን እና ሰሜን ሸዋ (ጨፉሮቢት፣ ሸዋሮቢት ማጀቴ፣
ኤፌሶን፣ አርጎባ) ፣ ዋግህምራ (ከትግራይ ከልል የሚዋሰኑ 27 የምርጫ ጣቢያዎች)
4. ደ/ብ/ብ/ህ/ ክልል - ጉራፈርዳ በአራት ቀበሌዎች፣ ሱርማ፣ ዘልማም (ግጭቶችን ተከትሎ
የምርጫ ተግባር መቀጠል መቻሉን የሚገልጽ መረጃ ባለመኖሩ)
በአጠቃላይ በጸጥታ ችግር የተነሳ የዘገዩ የምርጫ ጣቢያዎች ቁጥር 4,126 ነው ተብሏል፡፡
የመረጃ ክፍተት ፣ የጸጥታ መረጃ ( ክሊራንስ አለመኖር) ፣ የምርጫ ጣቢያዎች ጥበቃ ላይ ከፍተኛ ክፍተት መኖር ፣ ከምርጫ ጸጥታ ጋር በተያያዙ እንደ ዋና ችግር የተጠቀሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡