በርካታ ታሪኮች የተፈራረቁበት-ራስ ግንብ
ራስ ግንብ አጼ ፋሲል የጦር አበጋዛቸውና አማቻቸው ለነበሩት ለራስ ቢትወደድ ወልደጊዮርጊስ በ1636 ዓ.ም ያስገነቡት ነው
የ377 ዓመታት ዕድሜ ያለው ራስ ግንብ በአንድ ወቅት ለደርግ በመግረፊያ ማዕከልነት ያገለግል ነበር
በጎንደር ከተማ ከመድሃኒ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘው ታሪካዊው ግንብ አንደበት ቢኖረው ብዙ ይናገራል፡፡ ይህ ግንብ መጠሪያው ራስ ግንብ ሲሆን በ1636 ዓ.ም እንደተገነባ የታሪክ መዛግብቶችና አስጎብኝዎች ይገልጻሉ፡፡
ብዙ አሳዛኝና አስደሳች ክስተቶች በዚህ ግንብ ስር በመንግስት ትዕዛዝ ሰጭነት ተከናውነዋል፡፡
የ377 ዓመታት ዕድሜ ያለው ይህ ዕድሜ ጠገቡ ግንብ (ኪነ ሕንጻ) ፣ በደርግ ዘመነ መንግስት የሥርዓቱ አደጋ እንደሆኑ የሚጠረጠሩ ሰዎች ተሰብስበው ይገረፉበት ነበር፡፡
በወቅቱ በጎንደር የነበሩት ሻለቃ መላኩ ተፈራ እና የእርሳቸው ጓዶች ይህንን ግንብ የስርዓቱ ተቃዋሚዎች ናቸው ብለው ያሰቧቸውን የሚገረፉበት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የጎንደርና አካባቢዋ ነዋሪዎች ይህንን ግንብና ግቢውን በጥቅሉ መግረፊያ እንደሆነ እንጂ በተቃራኒው መልካም ተግባራት የተፈጸሙበት ፣ የራሶች መሰብሰቢያ እና በርካታ ውሳኔዎች የተላለፉበት ታሪካዊ ስፍራ እንደሆነ ብዙም እንደማያስታውሱት ይነገራል፡፡
የራስ ግንብ ሙዚየም አስጎብኚ ዘነብ ጥላሁን ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጸችው ፣ ደርግ የግንቡን የተወሰኑ ክፍሎች ለመግረፊያነት ይጠቀም ነበር፡፡ በዚህም ምክንየት በርካቶች ግንቡ ለመግረፊያነት ብቻ ያገለግል ይመስላቸው እንደነበርም አስጎብኚዋ ጠቅሳለች፡፡
ራስ ግንብ አጼ ፋሲል የጦር አበጋዛቸው እና አማቻቸው ለነበሩት ለራስ ቢትወደድ ወልደጊዮርጊስ ብለው በ1636 ዓ.ም ያስገነቡት እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ ራስ ቢትወደድ ወልደጊዮርጊስ ለአጼ ፋሲል ታማኝ በመሆናቸው ግንቡ እንደተገነባላቸው አስጎብኝዋ የታሪክ መዝገቦችን ጠቅሳ ገልጻለች፡፡
የጦር መሪዎች እና ነገስታት አብረው መቀመጥ ስላልነበረባቸው ከዋናው አብያተ መንግስት ወጣ ብሎ ነው ግንቡ የተገነባው፡፡
አጼ ፋሲል ሕንጻውን ለራስ ቢትወደድ ወልደጊዮርጊስ ቢያስገነቡትም ፣ ራስ ቢትወደድ ግን የኢትዮጵያ የጦር አዛዥ ስለነበሩ በየቦታው ስለሚዞሩ ሳይቀመጡበት በ1664 እንዳረፉ ይነገራል፡፡ ባለቤታቸው የአጼ ፋሲል ልጅ እስክንድራዊት ግን በዚህ ግንብ ውስት ይኖሩበት ነበር ተብሏል፡፡
በዚህ ግንብ ውስጥ የጎንደር ሹማምንት እና ራሶች ይቀመጡበት የነበረ ሲሆን ፣ ንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለስላሴ ወደ ጎንደር ሲሄዱ የሰሜኑ ጠቅላይ ግዛት አድርገው በቤተ መንግስትነት ይጠቀሙት እንደነበርም አስጎብኚዋ ትናገራለች፡፡ በዚህ ግንብ ውስጥ የጣሊያን ጄነራሎች እንደነበሩበትም ይነገራል፡፡
ራስ ግንብ ውስጥ ምን ይገኛል?
ግንቡ አራት ፎቆች ያሉት ሲሆን በውስጡም መመገቢያ ክፍል ፣ ማቀባበያ ክፍል ፣ የጸሎት ክፍልና በደርግ ዘመነ መንግስት ስርዓቱ ለመግረፊያነት ይጠቀምበት የነበረው ክፍል ይገኛሉ፡፡ የጎንደር ሹማምንት ፣ የንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለስላሴና የንግስት እቴጌ መነን መኝታ ከፍል የነበረ-ማምሻ ክፍል ፣ መናፈሻ ቴራስ ፣ ቀሳውስት ለነገሰታት ክብር የሚሰጡበት ከበሮ ቤት የሚባሉ ክፍሎችም አሉ፡፡
በተጨማሪም የራሶች መኝታ ቤት የነበረ እና በአጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ደግሞ ማንበቢያ ክፍል የተደረገ እንዲሁም የጣሊያን ጄነራሎች ጭምር ያነቡበት የነበረ ክፍልን ጨምሮ ሌሎች ቅርሶችም በራስ ግንብ ሙዚየም ይገኛሉ፡፡
የአጼ ፋሲል ግንብ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ሆኖ ሲመዘገብ ራስ ግንብን እንደ አንድ አካል አካትቶ ነው፡፡