በጎንደር በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ከፍተኛ ፍንዳታ ለመፈፀም በዝግጅት ላይ የነበሩ የጥፋት ቡድኖች ተያዙ፡፡
በጎንደር ዘንድሮ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በተኩስ የተቀናጀ ከፍተኛ ፍንዳታ ለመፈፀም በዝግጅት ላይ የነበሩ ሁለት የጥፋት ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተላከልኝ ያለውን መግለጫ ዋቢ አድርጎ ኢቢሲ እንደዘገበው በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ ዘንድሮ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በተኩስ የተቀናጀ ከፍተኛ ፍንዳታ ለመፈፀም የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በዝግጅት ላይ የነበሩ ሁለት የጥፋት ቡድን አባላት ከአራት ኤፍ ዋን ቦምብ እና ከ200 ጥይቶች ጋር ነው የተያዙት፡፡
ቡድኖቹ የተያዙት በብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ክትትል እንዲሁም በሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ በአማራ ክልል ፀጥታ ሀይሎች እና በአካባቢው ህብረተሰብ ትብብር ነው፡፡
ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የጥፋት ቡድን ያሰማራውን አካል በቀጣይ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የጥፋት ሀይሎቹ አደጋውን ቢያደርሱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እና መኖሪያ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚሰጣቸው ቃል የተገባላቸው መሆኑን እንዳረጋገጠ ገልጿል ።
የፀጥታ ሀይሎች ቀን ከለሊት በቁርጠኝነት በመስራታቸውና የህዝቡን ሰላምና ደህንነት በመጠበቃቸው በዘንድሮው የጎንደር የጥምቀት በዓል ታዳሚዎች ላይ ሽብር በመፈፀም የንፁሃንን ዜገች ህይወት ለመቅጠፍና በንብረት ላይ አደጋ ለማድረስ የታለመውን አደጋ ማክሸፍ መቻሉን ነው በመግለጫው የጠቆመው።
ዘንድሮ በመላው ሀገሪቱ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ተመሳሳይ ተልዕኮ ያላቸው አካላት እኩይ ተግባራቸውን ሊፈፅሙ ስሚችሉ ህብረተሰቡ በአካባቢው ከሚገኘው የፀጥታ ሀይል ጋር በመቀናጀት ከበዓሉ ጎን ለጎን ሰላሙንም እንዲጠብቅም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት አሳስቧል።
ምንጭ፡- ኢቢሲ