ህወሓት በባህርዳርና ጎንደር ሮኬት ተኩሶ ጉዳት ማድረሱን መንግስት አስታወቀ
ህወሓት በባህርዳርና ጎንደር ሮኬት ተኩሶ ጉዳት ማድረሱን መንግስት አስታወቀ
የፌደራል መንግስት ህወሓት በትናንትናው እለት በባህርዳርና ጎንደር ሮኬት መተኮሱንና በአውሮፕላን ማረፊያዎች አካባቢ ላይ መጠነኛ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል፡፡
ህወሓት “በእጁ ያሉትን የመጨረሻ መሳሪያዎች ጠጋግኖ” መሞከሩን የገለጸው መንግስት “ከመሞቱ በፊት የመጨረሻውን ዐቅሙን እየሞከረ መሆኑን ያመለክታል” ብሏል፡፡
የደረሰውን ጉዳት በሚመለከት መርማሪ ቡድን ተቋቁሞ እያጣራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ በጎደርና በባህርዳር ፍንዳታ መከሰቱን አረጋግጦ፣ ሁኔታው በጸጥታ ሀይሎች በቀጥጥር ስር መዋሉን አስታውቆ ነበር፡፡
ህወሓት የፌደራል መንግስት በአየር ጥቃት የሚፈጽም ከሆነ አውሮፕላኖቹ በሚነሱባቸው አየርማረፊያዎች ላይ ጥቃት እንደሚሰነዝር ገልጾ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥቅምት 24 ምሽት ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን ከገለጹ በኃላ በፌደራል መንግስትና በህወሓት መካከል የነበረው የቆየ አለመግባባት ተባብሶ ወደ ጦርነት አምርቷል፡፡
ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ የትግራይን ክልል የሚመራው ህወሓት ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲኖር ፍላጎቱን ቢገልጽም የፌደራል መንግስት “የህገወጡ የህወሓት” ቡድን ህግ ፊት ሳይቀርቡ ድርድር እንደማይኖር ገልጿል፡፡
የተወካዮች ምክርቤት የክልሉን መሪ ዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ብረሚካኤልን ጨምሮ የ39 የምክርቤት አባላትን ያለመከሰሰ መብት አንስቷል፡፡ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በህወሓት መሪዎች ላይ የፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ አውጥቶባቸዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ያለው አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት፣ ከመስራቾቹ አንዱ የነበረው ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ባለበት ወቅት ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ሃይሎች የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቁና ሰብአዊ መብትን እንዳይጥሱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡