የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለጎርጎራ አዲስ ማስተር ፕላን እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ
የጎርጎራ አካባቢ በገበታ ለሀገር ፕሮጄክት ይለማሉ ከተባሉ ሦስት ቦታዎች አንዱ ነው
አዲሱ ማስተር ፕላን የከተማዋን ታሪክ በጠበቀ መልኩ እንደሚዘጋጅ የዩኒቨርሰቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሥራት ገልጸዋል
ጎርጎራ እና ታሪኳ
ጎርጎራ ከባህርዳር በጣና 78 ኪሎ ሜትር ፣ ከጎንደር በአዘዞ 64 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከተማ ነች፡፡
ጎርጎራ በጣና ሀይቅ ደሴቶችና አካባቢው በሚገኙ ቀደምት ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሥልጣን ላይ የነበሩ የነገስታት አፅም፣ ቁሳቁሶች፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሰባሰቡ የታሪክ ቅርሶች የሚገኙባት ከተማ እንደሆነችም ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡ ቅርሶቹ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቀደምት የታሪክ ምስጢር መፍቻ ቁልፍ እንደሆኑም ተመራማሪዎቹ ያነሳሉ፡፡
ከ700 ዓመት በፊት ማለትም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጥንታዊቷን የጎርጎራ ደብረሲና ማርያምን ጨምሮ በርካታ ገዳማት በአካባቢው በመኖራቸው ምክንያት አርባ አራቱ የሚል ስያሜ ወጥቶላት እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። በአፄ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ፣ ማለትም ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ፣ በጎርጎራ ከተማና አካባቢዋ በተለይ በጣና ሀይቅ ውስጥ በሚገኙ ደሴቶች በርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት ታንጸዋል፡፡ አካባቢው አርባ አራቱ ጎርጎራ እየተባለ ይጠራ የነበረውም ከዚሁ ጋር በተገናኘ እንደሆነ ነው መዛግብቱ የሚገልጹት፡፡
ከጎርጎራ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተወሰኑት ዘመን ቢሻገሩም አብዛኛዎቹ በ16ኛው ክፍለ ዘመን መውደማቸው ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያ ያስተናገደቻቸው ተደጋጋሚ ጦርነቶች አብያተ ክርስቲያናቱ እንዲወድሙ አድርጓቸዋል ነው የሚባለው፡፡
በ1312 ዓ.ም የተመሰረተችውና በ2012 ዓ.ም 700ኛ ዓመት የምስረታ በዓሏን ያከበረችው “የደብረሲና ማርያም” አንድነት ገዳም አርባ አራቱ ጎርጎራ ተብለው ከሚጠሩት ውስጥ አንዷ ናት። “የደብረሲና ማርያም” አንድነት ገዳምን ያሰሯት የአፄ አምደ ጽዮን የጦር አዛዥ ኤስድሮስ ሲሆኑ ደብረሲና ማርያም የተባለችው የኤስድሮስ ትውልድ ስፍራ ደብረሲና በመሆኑ ነው የሚሉ አሉ፡፡
ደብረሲና ማርያም በጣና ሀይቅ ዳርቻ የተመሰረተች በመሆኗ የጎንደር ነገስታት መዳረሻ እንደነበረች ይነገራል። በጎርጎራ በምትገኘው ደብረሲና ማርያም አንድነት ገዳም ከ350 ዓመታት በላይ ያለ እድሳት የኖሩ ሥዕሎች፤ የብራና መጽሐፍት ትናንትን ያሳያሉ፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ ገዳሟ 78 ሄክታር የሚሆን የይዞታ መሬት የነበራት ቢሆንም በደርግ መንግሥት ይዞታዋን ተነጥቃለች። ከ1983 ዓ.ም በኋላ ደግሞ የገዳሟ ይዞታ በግለሰቦች ይዞታ ስር እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
አዲሱ የጎርጎራ ከተማ ማስተር ፕላን
ነሐሴ 2012 ዓ.ም ይፋ በተደረገው የ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጄክት ከሚለሙ ሦስት ስፍረዎች መካከል አንዷ ከ700 ዓመት በላይ ያስቆጠረችው የጎርጎራ ከተማ ስትሆን ከተማዋ የነገስታት መናገሻ እስከመሆን ብትደርስም የሚገባትን የከተማነት ልማት ሳታገኝ ቀርታለች፡፡ ይህንን ለመቅረፍና ከተማዋን በአዲስ መልክ ለመገንባት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለጎርጎራ አዲስ ማስተር ፕላን እያዘጋጀ ነው፡፡ የዩኒቨርሰቲው ፕሬዝዳንት አሥራት አጸደወይን (ዶ/ር) ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ የጎርጎራ ከተማ አዲስ ማስተር ፕላን የረጅም ጊዜ ልምድ ባላቸው አርክቴክቶች እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕላኑ የሚዘጋጀው የአካባቢውን ባሕል፣ እሴትና እምነትን ከግምት አስገብቶ እንደሆነም ነው ዶ/ር አሥራት የጠቀሱት፡፡ በዚህ የማስተር ፕላን ሥራ ውስጥ ከአርክቴክቸር ባለሙያዎች በተጨማሪ በልምዳቸውና በትምህርት ዝግጅታቸው የተመረጡ የታሪክ፣የአንትሮፖሎጅ፣ ኢኮሎጅ ፣ የባህል ተመራማሪዎች መካተታቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስታውቀዋል፡፡
ማስተር ፕላኑን የሚያዘጋጁት “ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ 36 ባለሙያዎች ናቸው” ያሉት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት “ሀሳባችን ማስተር ፕላኑን በዚህ በጀት ዓመት መጨረሻ ለማስረከብ ነው” ብለዋል፡፡
በአርክቴክትና መሰል ሙያ ለይ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚፈልጉ ባለሙያዎችም ከዩኒቨርሲቲው ጋር መነጋገር እንደሚችሉ ነው ፕሬዝዳንቱ ያነሱት፡፡
የ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጄክት አካል የሆነችው ጎርጎራ በቀጣይ ዘመናዊ ከተማ እንድትሆን ለማድግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ዶ/ር አሥራት ገልጸዋል፡፡
የገበታ ለሀገር ፕሮጄክት የከተማዋ ቀጣይ ዕድል የሚወሰንበት ትልቅ አጋጣሚ ስለሆነ ሁሉም ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡