ሰርጂዮ ራሞስ ከ16 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከሪያል ማድሪድ ጋር ሊለያይ ነው
ራሞስ በአውሮፓውያኑ 2005 በ27 ሚሊየን ዩሮ ነው ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው
4 የቻምፒየንስ ሊግ፣ 5 የላሊጋ እና 2 የኮፓ ዴል ሬይ ዋናጫዎችን ከማድሪድ ጋር ማንሳት ችሏል
የሪያል ማድሪድ አምበል ሰርጂዮ ራሞስ ከ16 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከክለቡ ጋር ሊለያይ መሆኑ ተሰምቷል።
ከሪያል ማድሪድ ጋር 22 ዋንጫዎችን ማንሳት የቻለው ተከላካዩ ሰርጂዮ ራሞስ በነገው እለት ሽኝት እንደሚደረግለትም ክለቡ አስታውቋል።
በሽኝት መርሃ ግብሩ ላይ የሪያል ማድሪድ ፕሬዚዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔርዝ እንደሚገኙ ክለቡ ገልጿል።
የ35 ዓመቱ ሰርጂዮ ራሞስ በመገባደድ ላይ ባለው የውድድር ዘመን ከጉዳት ጋር እየታገለ ሲሆን፤ የውድድር ዓመቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ 5 ጨዋታዎች ላይ ብቻ ነው ለክለቡ የቻለው።
ሰርጂዮ ራሞስ በአውሮፓውያኑ 2005 ለሪያል ማድሪድ በ27 ሚሊየን ዩሮ የፈረመ ሲሆን፤ በወቅቱ ለስፔናዊው ተከላካይ የተከፈለው ገንዘብ ክብወሰን የሰበረ እንደነበረ ይታወሳል።
ራሞስ በሪያል ማድሪድ በነበረው የ16 ዓመታት ቆይታው 671 ጨዋታዎች ላይ የተሳተፈ ሲሆን፤ 101 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
ራሞስ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጥር ከ2015 ጀምሮ የሪያል ማድሪድ አምበልነት ስፍራን ከክለቡ ግብ ጠባቂ ኤከር ካሲያስ እጅ መረከቡ አይዘነጋም።
ሰርጂዮ ራሞስ በሪያል ማድሪድ ውስጥ ስኬታማ ከሚባሉ ተጫዋቾች አንዱ ነው የተባለ ሲሆን፤ ከክለቡ ጋር በነበረው ቆይታም 4 የቻምፒየንስ ሊግ፣ 5 የላሊጋ እና 2 የኮፓ ዴል ሬይ ዋናጫዎችን ማንሳት ችሏል።
ተከላካዩ ሰርጂዮ ራሞስ በ2020 የአውሮፓ ዋንጫ ላይ እየተሳተፈ ከሚገኘው የስፔን ብሄራዊ ቡድን ስብስብ ውጪ መደረጉም ይታወሳል።
ተጫዋቹ በስፔን ብሔራዊ ቡድን ውስጥም በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል ፤ በ180 ጨዋታዎች ላይ ሀገሩን ወክሎ በመሳተፍ 23 ጎሎችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
ስፔንን በመወከልም በ4 የዓለም ዋንጫዎች እና በ3 የአውሮፓ ዋንጫ ውድድሮች ላይ የተሳተፈ ሲሆን፤ የ2010 የዓለም ዋንጫን እንዲሁም የ2008 እና የ2012 የአውሮፓ ዋንጫን ባነሳው የስፔን ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ ጉልህ ሚና የነበረው ተጫዋች ነው።