የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በክፍት መኪና በመሆን ከደጋፊዎች ጋር ደስታቸውን እየገለጹ ነው
የዓለም ዋንጫ አሸናፊው የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በዛሬው እለት በዋና ከተማው ቦነስ አይረስ ዳርቻ በሚገኘው ኢዜዛ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሷል።
ቡድኑ ከአውሮፕላን የወረደው በቡድኑ መሪ ሊዮኔል ሜሲ እየተመራ እና ወርቃማውን የዓለም ዋንጫን በመያዝ ነበር።
የቡድኑ አባላት ወደ አርጀንቲና እግር ኳስ ማህበር ማሰልጠኛ ማእከል በሚሄድ አውቶቡስ ከመሳፈራቸው በፊት ቀይ ምንጣፍ በእግራቸው ተጉዘዋል።
በመቀጠልም በዋና ከተማዋ በክፍት መኪና በመሆን ከደጋፊዎች ጋር ደስታቸውን በማጣጣም ላይ ይገኛሉ።
ምንም እንኳን ብሄራዊ ቡድኑ ቦነስ አይረስ የደረሰበት ሰዓት ለሊት ቢሆንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርጀንቲናውያን በአደባባይ ወጥተዋል ።
የዛሬው ዕለት በአርጀንቲና ብሄራዊ የደስታ ቀን ተብሎ መታወጁ ይታወሳል።
በኳታር የዓለም ዋንጫ እሁድ ሲጠናቀቅ በሊዮኔል ሜሲ የሚመራው የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድን ፈረንሳይን በመርታት ዋንጫውን ማንሳት ችሏል።
አርጀንቲና ማሸናፏን ተከትሎም የሊዮኔል ሜሲ ሀገር ለ3ኛ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ማንሳት ችላለች።
ሊዮኔል ሜሲ ከ36 አመት በፊት ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና ያሳካውን ክብር በደገመበት ምሽት የብራዚላዊውን ፔሌ የጎል አስቆጣሪነት ክብር ማሻሻል ችሏል።