ካርሎ አንቸሎቲ አምስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ያነሱ አሰልጣኝ በመሆን አዲስ ታሪክ አጽፈዋል
ሪያል ማድሪድ የጀርመኑን ቦርሺያ ዶርትሙንድ በማሸነፍ 15ኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን አነሳ።
ማድሪድ በምሽቱ የዌምብሌይ የፍጻሜ ጨዋታ ዳኒ ካርቫሃል በ74ኛው፤ ቪንሺየስ ጁኒየር በ83ኛው ደቂቃ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ነው ለድል የበቃው።
የኤዲን ቴርዚች ቡድን በመጀመሪያው አጋማሽ የፈጠራቸውን የጎል እድሎች መጠቀም አለመቻሉ ዋጋ አስከፍሎታል።
በተለይ ካሪም አድየሚ ሁለት የጎል እድሎችን ያመከነበት አጋጣሚ በድጋፍ ድምጻቸው ዌምብሌይን ላደመቁት የዶርትሙንድ ደግፊዎች የሚያስቆጩ ነበሩ።
የሪያል ማድሪዱ ግብ ጠባቂ ቲቦ ኮርትዋ የዶርትሙንድን አጥቂዎች ሙከራ በማክሸፍ ለቡድኑ ድል ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ዶርትሙንድ በዌምብሌይ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ ሲሸነፍ የትናንት ምሽቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የቡንደስሊጋው ክለብ በፈረንጆቹ 2013 ከባየርሙኒክ ጋር ለፍጻሜ ተገናኝቶ መሸነፉ ይታወሳል።
በአንጻሩ ሪያል ማድሪድ በሻምፒዮንስ ሊጉ በርካታ ዋንጫዎችን በማንሳት ቀዳሚነቱን የሚያጠናክር ውጤት አስመዝግቧል።
15ኛ የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫውን ያነሳው ማድሪድ የሚከተለውን ኤሲ ሚላን በስምንት ዋንጫዎች ይበልጣል።
አሰልጣኝ ካርሎ አንቼሎቲም ትልቁን ዋንጫ አምስት ጊዜ በማንሳት አዲስ ታሪክ አጽፈዋል።
ጣሊያናዊው አሰልጣኝ በ2003 እና 2007 ከኤሲ ሚላን ጋር በ2014, 2022 እና 2024 ደግሞ ከማድሪድ ጋር ዋንጫውን ማንሳት ችለዋል።
በተጫዋችነት ዘመናቸው በ1989 እና 1990 የያኔውን የዩሮፓ ካፕ የአሁኑን ሻምፒዮንስ ሊግ ያነሱት ካርሎ አንቼሎቲ በአምስቱ ዋናዋና የአውሮፓ ሊጎች ዋንጫ ያሳኩ ብቸኛው አሰልጣኝም ናቸው።