ምባፕ የፈረመው ኮንትራት በሳንቲያጎ በርናባው እስከፈረንጆቹ 2029 ድረስ ያቆየዋል
ክሊያን ምባፔ ለሪያል ማድሪድ መፈረሙ ተገለጸ።
የፈረንሳዩ አምበል እና የፓሪስ ሴንት ጄርሜን(ፒኤስጂ) አጥቂው ክሊያን ምባፔ በሪያል ማድሪድ ክለብ ለአምስት አመት የሚያቆየውን መፈረሙን የስፔኑን 'ማርካ' ጋዜጣ ጠቅሰው በርካታ የእንግሊዝ ጋዜጦች ዘግበዋል።
ምባፔ ኮንትራቱ እንደተጠናቀቀ ፒኤስጂን መልቀቅ እንደሚፈልግ ያሳወቀው ባለፈው ሳምንት ነበር።
የ25 አመቱ ምባፔ በዚህ የጨዋታ ዘመን(ሲዝን) መጨረሻ ኮንትራቱ ሲጠናቀቅ በነጻ ዝውውር ፒኤስጂን ይለቃል ተብሏል።
ተጨዋቹን ለማስፈረም አርሰናል እና ሊቨርፑል ፍላጎት ማሳየታቸው ቢገለጽም፣ ሪያል ማድሪድ ከሁለት ሳምንት በፊት የማስፈረሙን ውድድር አሸንፋል ተብሏል።
ምባፕ የፈረመው ኮንትራት በሳንቲያጎ በርናባው እስከፈረንጆቹ 2029 ድረስ ያቆየዋል። ሪያል ማድሪድ ወደ ክለቡ ሲቀላቀል 85.5 ሚሊዮን ዩሮ ይሰጠዋል ተብሏል።
ምባፔ ጁዴ በሊንግሃምን በመብለጥ የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ ይሆናል።
በድርድር ወቅት ተጨዋቹ በአንድ የጨዋታ ዘመን 42.8 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 827 ሺ ዩሮ ሳምንታዊ ደሞዝ እንዲከፈለው የጠየቀ ቢሆንም የሪያል ማድሪድ ባለስልጣናት ግን ቁጥሩ ዝቅ እንዲል ፈልገዋል።
ሪያል ማድሪድ ምባፔ በሞናኮ ሲጫወት ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ለማስፈረም ፍላጎት አሳይቶ ነበር።
በፈረንጆቹ 2022 ሪያል ማድሪድን ለመቀላቀል መቃረቡ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም በፒኤስጂ የነበረውን ኮንትራት በሁለት አመት ማራዘሙን ማስታወቁ ይታወሳል።
በዚያው አመት ከሳኡዲ ፕሮ ሊጉ የ259 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም ምባፔ ሳይቀበለው ቀርቷል።
ክለቡ ሪያል ማድሪድ በምባፔ መዛወር ጉዳይ እስካሁን በይፋ ያለው የለም ተብሏል።
የ2018ቱ የአለም ዋንጫ ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አባል የነበረው ምባፔ በ222 ሚሊዮን ዩሮ ከተቀላቀለው ብራዚላዊዉ ኔይማር ቀጥሎ በ94 ሚሊዮን ዶላር ሁለተኛ ውድ ተከፋይ ሆኖ ነበር በ2017 ከሞናኮ ወደ ፒኤስጂ የተቀላቀለው።
ፒኤስጂ አምስት የሊግ ዋን ድሎችን እንዲያገኝ ያደረገው የ25 አመቱ አጥቂ በ290 ጨዋታዎች ተሰልፎ 243 ግቦችን አስቆጥሯል። ምባፔ የክለቡ የምንግዜም ግብ አስቆጣሪ በመሆን እየመራ ነው።