“ትግራይን የተመለከተው ሰሞነኛው የተመድ መግለጫ ከዚህ ቀደም ሲንጸባረቁ የነበሩ አስተያየቶችን ያጠፈ ነው”- አምባሳደር ዲና
መግለጫው “መንግስት ምንም እያደረገ አይደለም በሚል የሚቀርቡ ክሶችን የሚያፈርስ” እንደሆነም ነው አምባሳደር ዲና የተናገሩት
ተመድ በመግለጫው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጠበቀ መልኩ የጋራ መፍትሔ ያስፈልጋል ማለቱንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል
ትግራይን የተመለከተው ሰሞነኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መግለጫ “ከዚህ ቀደም በተለይም በምዕራቡ ዓለም ሲንጸባረቁ የነበሩ ስሜቶችንና አስተያየቶችን ያጠፈ ነው” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ዲና የሚኒስቴሩን ሳምንታዊ የስራ ክንውኖች በማስመልከት መግለጫን ሰጥተዋል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት መግለጫ መንግስት ሰብዓዊ ርዳታዎችን ለማቅረብ እያደረገ ላለው ጥረት እውቅና እንደሚሰጥ በመግለጫቸው የጠቆሙት ቃል አቀባዩ “እውቅናው መንግስት ምንም እያደረገ አይደለም በሚል የሚቀርቡ ክሶችን የሚያፈርስ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በጠበቀ መልኩ የጋራ መፍትሔ ያስፈልጋል የሚል ነገር በመግለጫው አስቀምጧል፡፡
የረድዔት ተቋማት የሰብዓዊነት መርሆዎችን በጠበቀ መልኩ የሚያደርጉትን ርዳታ ያሳድጉ የሚል መልዕክትም አለው፡፡
“የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና አንድነት በጠበቀ መልኩ ሁሉንም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል” ይላልም መግለጫው፡፡
ይህ “ምክር ቤቱ ከሞላ ጎደል ሚዛናዊ እና እስካሁን በእኛ በኩል ስንለው የነበረውን ነገር ያስተጋባበት ነው” ያሉት አምባሳደር ዲና “ከዚህ በፊት በአንዳንድ ወገኖች ይቀርብ የነበረውን የተዛባ አመለካከት በተመለከተ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለውን አተያይ የቀየረ ነው” ለማለትም ይቻላል ብለዋል፡፡
መግለጫው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከአፍሪካ ህብረት እና ከተመድ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር አሉ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማጣራት ለሚያደርጋቸው ጥረቶች እና ዝግጅቶች እቀውቅና የሚሰጥ እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ እና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በኩል ምርመራዎችን እያደረገች ስለመሆኗ ቀደም ሲል አስታውቃለች፡፡
ይህ “መንግስት ጥፋተኞችን ለህግ የማቅረብ የጸና ፍላጎት እንዳለው ያሳያል” ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
አምባሳደር ዲና ኢትዮጵያ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክ ሼስኬዲ የግድቡን ድርድር ዳግም እንዲያስጀምሩ ፍላጎት እንዳላትም ተናግረዋል።
ይህንኑ ፍላጎት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር እያሳወቀች እንደምትገኝም ነው የጠቆሙት።
ኢትዮጵያ የግድቡ ጉዳይ “በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር ይፈታ” የሚል ጽኑ አቋም እንዳላት ደጋግማ ለጸጥታው ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ጭምር አሳውቃለች፡፡
ሆኖም ግብጽ እና ሱዳን ድርድሩ ከህብረቱ በተጨማሪ ሌሎችንም አካላት እንዲያካትት ይፈልጋሉ፡፡
ይህ ፍላጎት ድርድሩ ከአፍሪካ እንዲወጣ ለማድረግ መሆኑንም ነው “በጉዳዩ ላይ እየሰሩ ነው”ያሉት አምባሳደር ዲና የተናገሩት።