የሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር ሙሌት ከተከናወነ ሱዳን በኢትዮጵያ እና በሳሊኒ ላይ ክስ እንደምትመሰርት ገለጸች
ሁለተኛው ዙር የግድቡ ሙሌት በምንም መልኩ እንደማይቀር ኢትዮጵያ መግለጿ ይታወቃል
የሱዳኑ የውሃ ሚኒስትር “ክሱ የሚመሰረተው ግድቡ በሚያስከትላቸው ተፅእኖዎች ላይ ጥናት ባለመደረጉ ነው” ብለዋል
የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ያለሕጋዊ ስምምነት የሚከናወን ከሆነ ፣ የግድቡን የሲቪል ግንባታ ማከናወን ላይ በሚገኘው የጣሊያን ኩባንያ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ክስ እንደምትመሰርት ሱን ዝታለች፡፡
የሱዳን የመስኖ እና የውሃ ሀብት ሚኒስትር ያሲር አባስ "ሁለተኛው ሙሌት ሕጋዊ ስምምነት ሳይደረስ የሚከናወን ከሆነ ፣ ሱዳን በጣሊያኑ ኩባንያ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ክስ የሚመሰርቱ በዓለም አቀፍ የሕግ ቢሮዎች የሚደገፉ የሕግ ቡድኖች አሏት" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
አክለውም “ክሱ የሚመሰረተው ግድቡ በሚያስከትላቸው አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተፅእኖዎች እና አደጋዎች ላይ ጥናት ባለመደረጉ ነው” ብለዋል ፡፡
ሚኒስትሩ “ስምምነት ላይ አለመደረሱ ፣ ግድቡ በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ ላይ ስጋት በመደቀኑ ለተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ም/ቤት አቤቱታ ለማቅረብ መንገድ የሚከፍት” መሆኑን አመልክተዋል ፡፡
“ስምምነት ላይ መድረስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ወይም መብት አይቀንስምም ፤ ነገር ግን የሱዳንን ሙሉ መብት ይሰጣል እንዲሁም ጥቅም ያስጠብቃል” ብለዋል አባስ፡፡
በግድቡ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ከአፍሪካ ሕብረት በተጨማሪ የተባበሩት መንግስታት ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና አሜሪካ እንዲያሸማግሉ ጥሪ ብታቀርብም ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ቀመር ውድቅ ማድረጓ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣዩ የክረምት ወቅት ሁለተኛውን ዙር 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመሙላትን ሂደት እንደምትቀጥል በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የግድቡን ኮሪደር (ውሃው የሚወርድበትን መሀለኛውን ክፍል) ለመገንባት በሁለት ተርባኞች አማካኝነት ከግድቡ ውሃ የማስተንፈስ ስራ ተከናውኗል፡፡ የኢትዮጵያ የውሃ ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ፣ ሁለተኛው ዙር የግድቡ ሙሌት በምንም መልኩ እንደማይቀር መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ ባለፈው ዓመት በመጀመሪያ ዙር 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መሞላቱ የሚታወስ ነው፡፡