14 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ፈጽመዋል ከተባሉት ተጠርጣሪዎች መካከል አራቱ መያዛቸውን ክልሉ አስታውቋል
14 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ፈጽመዋል ከተባሉት ተጠርጣሪዎች መካከል አራቱ መያዛቸውን ክልሉ አስታውቋል
ከትናንት በስቲያ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ ጥቃት በመፈጸም ሰዎችን ገድለዋል ከተባሉ ግለሰቦች መካከል አራቱ መያዛቸውን የክልሉ ሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ አስታውቋል፡፡
በጥቃቱ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩ 14 የአማራ ተወላጆች መሞታቸውን የአማራ ክልል መንግስት አስታውቋል፡፡ ክልሉ በነዋሪዎቹ ህይወት ማጣት ሀዘኑን ገልጾ፤ ይህን ያደረጉት ከለውጡ በተቃራኒ የቆሙ ሰዎች መሆናቸውን ገልጿል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ መሀመድ እንደገለጹት የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ድርጊቱን የፈጸሙትን ግለሰቦች ለመያዝ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
እስካሁንም አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለጹት አቶ አብዱላዚብ ቀሪ ወንጀለኞችን ይዞ እርምጃ ለመውሰድ የክልሉ መንግስት ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡ ቀደም ብሎም በአካባቢው ሠላምን ለማረጋገጥ እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን አቶ አብዱላዚዝ አስታውቀዋል፡፡
ጥቃቱን ያደረሱት የጥፋት ቡድኖች ናቸው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተገቢ ስልጠናና ተልዕኮ በመያዝና በከባድ መሳሪያ በመታገዝ የብሔር ግጭት የመቀሰቀስ ዓላማ በመያዝ ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራ ሲያደርግ መቆየቱንም መናገራቸውን የክልሉን መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡
ባለፉት ሶስት አመታት በኢትዮጵያ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰፍረው ቆይተው ነበር፡፡ የክልሉ መንግስት ባለፈው ግንቦት ወር አብዛኞቹን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሱን አስታውቆ ነበር፡፡