እየተያዘ ያለው ሀሰተኛ ብር “ሀይ ኮፒ” እንጅ “ፎርጅድ” አይደለም፡ የአማራ ክልል መንግስት
በክልሉ እስካሁን 300ሺ ሀሰተኛ የብር ኖት መያዙን ኃለፊው ግዛቸው ተናግረዋል
ግለሰቦች ሀሰተኛ የብር ኖት ወደ ገጠር አካባቢ ይዘው በመሄድ በከብትና እህል ሽያጭ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ለማጭበርበር ተንቀሳቅሰዋል
ግለሰቦች ሀሰተኛ የብር ኖት ወደ ገጠር አካባቢ ይዘው በመሄድ በከብትና እህል ሽያጭ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ለማጭበርበር ተንቀሳቅሰዋል
በአማራ ክልል በጸጥታ አካላት እየተያዘ ያለው ሀሰተኛ የብር ኖት “ሀይ ኮፒ” ወይም አንደኛ ደረጃ ቅጅ እንጅ ተመሳስሎ የተሰራ “ፎርጅድ” የብር ኖት አለመሆኑን የክልሉ መንግስት ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት የብር ኖቶች ቅያሬ ማድረጉን ይፋ አድርጎ ነበር፤ ቅያሬውን ተከትሎ በአማራ ክልል በተለያየ ጊዜ አዲሶቹን የብር ኖቶች በሚመስሉ ሀሰተኛ የብር ኖቶች ለመቀየር ሲንቀሳቀሱ ግለሰቦችን መያዙን በተከታታይ እያሳወቀ ይገኛል፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ለአል ዐይን ኒውስ እንደገለጹት በቅርቡ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች እየተያዙ ያሉት ሀሰተኛ የብር ኖቶች “ፎርጅድ ተብለው የሚገለጹ አይደሉም፤ ፎርጅድ ተመሳስሎ የሚሰራ ነው” ብለዋል፡፡
ኃላፊው ትክክለኛውን የብር ኖት በቀላሉ በማንኛውም ስካን መሳሪያ ኮፒ በማድረግ በህገወጥ መንገድ እየተሰራጨ መሆኑን የገለጹ ሲሆን ከባንክ ውጭ በሚደረግ ቅያሬ መታለል ሊጋጥም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
“አሁን ላይ አዲስ ስለሆነ በተለይ 10 ብር፤ የ50 ብር የ100 ብር ኖቶች በማመሳስል ተመሳሳይ ብር በአንደኛ ቅጅ/ሃይ ኮፒ/ በማድረግ ነው ለቀየር ነው እየተሞከረ ያለው” ብለዋል ኃላፊው፡፡
አቶ ግዛቸው ኮፒ የተደረገውን ብር ወደ ገጠር አካባቢ በመሄድ በከብትና እህል ሽያጭ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን ለማጭበርበር መሞከሩን ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በክልሉ በአጠቃላይ ወደ 300ሺ የሚጠጋ ሀሰተኛ ብር መያዙን የገለጹት ኃላፊው ፖሊስ ሀሰተኛ የብር ኖት ይዘው የተገኙ ሰዎች መያዙን ተጠቅሷል፡፡ የሀሰተኛ የብር ኖቱን ምንጭ በተመለከተ ላነሳንላቸው ጥያቄ ኃላፊው “ፎርጀሪ ቢሆን ምንጩን ለማወቅ ጥረት ይደረጋል፤ ነግርግን በኮፒ ማሽን የትኛውም ቦታ ሊታተም ይችላል” የሚል መልስ ሰጥተውናል፡፡
“በእጁ አዲሱን ብር ይዞ የሚያውቅ ሰው አይሸወድም፤ ምክንያቱን ሃሰተኛው ብር ከትክክለኛው የብር ኖት የሚለይበት ገጽታ አለው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኮፒው በውሃ ሲነካ ቀለሙ የመልቀቅ ባህሪም አለው፡፡”
አዲሱን ብር አይቶ የማያውቅ በተለይም አርሶ አደር እንዳይታለል በማሰብ ከባንክ ውጭ ከግለሰብ ብር መየቀየር እንደማይገባ አሳስበናል ብለዋል ኃላፊው፡፡
አቶ ግዛቸው በክልሉ እስካሁን በስድስቱ ዞኖች የሃሰተኛ ብር መያዙ መያዛቸውን የገለጹ ሲሆን ማኅበረሰቡ በሀሰተኛ ብር እንዳይሸወድ በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች ያሉ የንግድ ባንክ ሃላፊዎችንና የየወረዳውን የኮሚኒኬሽን ሃላፊዎች በማሰማራት የማንቃት ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡
አቶ ግዛቸው እንዳሉት ሰው በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ቤተክርስቲያንንና መስጅድን ጨምሮ በብቅያሬው ዙሪያ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡
ይህን ተከትሎም ከህብተሰብ በርካታ ጥቆማ በመምጣቱ እስካሁን በትንሹ ሀሰተኛ የብር ኖት ይዘው የተገኙ በትንሹ 10 ሰዎቸ በፖሊስ መያዛቸውን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል፡፡
ከባንክ ውጭ እየተዘዋወረ ያለው ብር ወደ ባንክ እንዲገባ ለማድረግና ሙስናን ለመከላከል መንግስት የብር ኖት ለመቀየር እንደምክንያት አስቀምጦ ነበር፡፡በቅያሬውም በ3.7ቢሊዮን ብር ወጭ 2.9 ቢሊዮን የብር ኖቶች ማተሙን መግለጹ ይታወሳል፡፡