ከ1. 5 ሚሊየን ብር በታች የሆነ ገንዘብ በህገ ወጥነት መያዝ እንደሌለበት ተገለፀ
ገንዘባቸውን በተለያዩ ባንኮች ሂሳብ በመክፈት በማስቀመጥ ማጭበርበር የሚሞክሩትን የሚከታተል ግብረ ሀይል ተቋቁሟል
ከፍተኛ ሽያጭ የሚያከናውኑ ተቋማት በሚይዙት የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ አለመቀመጡም ተገልጿል
ከ1. 5 ሚሊየን ብር በታች የሆነ ገንዘብ በህገ ወጥነት መያዝ እንደሌለበት ተገለፀ
የፀጥታ ኃይሎች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በታች የሆነን ገንዘብ በህገ ወጥነት መያዝ እንደሌለባቸው ተገለፀ።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ እና የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) በዛሬው እለት አዲሱን የብር ኖት ለውጥ ተከትሎ መግለጫ መስጠታቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል።
በመግለጫው ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ፣ ከብር ኖት ለውጡ ጋር በተያያዘ የተወሰነ ውዥንብር መፈጠሩን ገልጸዋል።
በዚህም የፀጥታ ሀይሎች በመቶ ሺዎች ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሰዎችን እየያዙ መሆኑን እና ይህም ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው እስከ 1 ነጥብ 5 ሚልየን ብር ያላቸው ሰዎች ያለመሳቀቅ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ መያዝን የሚከለክለው መመሪያ እንደ ነዳጅ ማደያ እና ሌሎች ከፍተኛ ሽያጭ የሚያከናውኑ ተቋማትን እንደማይመለከትም ተጠቅሷል።
ነገር ግን ባለሀብቶች በእነዚህ ተቋማት በኩል ገንዘባቸውን በዚህ መንገድ እናስገባለን ብለው ከሞከሩ የንግድ ተቋማቱ የሽያጭ ታሪካቸው ክትትል ስለሚደረግበት እንዳይሞክሩትም አሳስበዋል።
አንዳንድ ግለሰቦች መመሪያው ባንክ ብቻን የሚመለከት ነው በሚል በርከት ያለ ገንዘብ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በኩል ለማስገባት ሙከራ እያደረጉ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፣ መመሪያው ለባንኮችም ለማይክሮ ፋይናስ ተቋማትን እኩል የሚያገለግል መሆኑ ተነስቷል።
በተለያዩ ባንኮች ሂሳብ በመክፈት ገንዘብ በትኖ ለማስቀመጥ የሚሞክሩ ካሉም ይህንን የሚቆጣጠር ግብረ ሀይል መቋቋሙ እና ይህንን ተግባር ፈጽሞ በተገኙት ላይ ብራቸውን እስከ መውረስ የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተነስቷል።
እንዲሁም በተለያዩ ሰዎች አማካኝነት ገንዘብ ማስቀመጥ እንዲሁም በሌላ ሰው ስም ገንዘብ ማስገባት እንደማይቻልም በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
ከአሽከርካሪዎች ጋር በተያያዘም ከጎረቤት ሀገራት በተለይ ከጅቡቲ ጋር በተያያዘ አሽከርካሪዎች ገንዘብ ይዘው ስለሚንቀሳቀሱ ፣ ሁሉም ገንዘብ ህገ ወጥ ነው ተብሎ መያዝ እንደሌለበት በመግለጫው ተጠቅሷል።
አሽከርካሪዎች ከሀገር ሲወጡ እስከ 30 ሺህ ብር ይዘው መውጣት እንደሚችሉ፤ ሲገቡ ደግሞ እስከ 10 ሺህ ብር መያዝ የሚችሉ መሆኑም ታውቋል።
ሆኖም ግን በህገ ወጥ መንገድ ብር በተሽከርካሪያቸው ውስጥ ደብቀው ለማስገባት የሚመክሩ ካሉም እንደሚወረስባቸው የኤፍቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
የብር ኖቶች መቀየራቸው በተነገረበት ወቅት በህገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀስ ገንዘብን የጸጥታ ኃይሎች በጥብቅ ክትትል እንዲይዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ማሳሰባቸው ይታወቃል፡፡ የጸጥታ ኃይሎች የሚይዙትን ገንዘብ ለየተቋማቸው ማጠናከሪያነት እንዲጠቀሙም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈቃድ ሰጥተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብ በቁጥጥር ስር እየዋለ መሆኑን የተመለከቱ ዘገባዎች ትናንትና ዛሬ መውጣታቸው ይታወቃል፡፡