ድምጻዊት ቪሮኒካ አዳነ በህመም ምክንያት በዳላስ የሙዚቃ ዝግጅቷን አቋረጠች
አሜሪካ የምትገኘው ድምፃዊቷ በህመም ምክንያት ዝግጅቶቿን ማቅረብ እንዳልቻለች ተናግራለች
ቪሮኒክ በአሁኑ ሰአት የህክምና ክትትል እየተደረገላት ይገኛል
በተለያዩ ነጠላ ዜማዎቿ ተወዳጅነትን ያተረፈችው ድምጻዊት ቪሮኒካ አዳነ በህመም ምክንያት በዳላስ የሙዚቃ ዝግጅቷን አቋረጠች።
ድምጻዊት ቪሮኒካ አዳነ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች በመዘዋወር የሙዚቃ ስራዎችን በማቅረብ ላይ ነበረች።
ሆኖም ግን ባጋጠማት የጤና እክል ምክንያት ሆስፒታል በመግባቷ የሙዚቃ ስራዋን ማቋረጠቷን በይፋዊ የኢንስተግራም ገጿ ላይ አስታውቃለች።
“ትናንት ህዳር 15 ዳላስ ላይ ሾ እንዳለኝ አሳዉቄ ነበር” ያለችው ቬሮኒካ “ፎቶ ላይ እንደምታዩት ከባድ ነገር ቢያጋጥመኝም ዳላስ ላይ የምትገኙ ቤተሰቦቼን ላለማስከፋት ቦታዉ ላይ ተገኝቼ ነበር፤ ለመዝፈን ብሞክርም ለመዝፈን አልቻልኩም" ብላለች።
ቬሮኒካ" ዳላስ የሚገኙ ኢትዮዽያዉያን እና ኤርትራዉያንም ቦታዉ ላይ መገኘቴን ብቻ ተረድተዉ መናገር ከምችለዉ በላይ ፍቅር እና ክብር ሰተዉኝ ቆንጆ ጊዜ አብረን አሳልፈናል; መጨረሻ ላይም የአቅሜን 6; 7 ዘፈን ተጫዉቼ ወርጃለዉ" ብላለች።
ዳላስ የሚገኙ አድናቂዎቿንም ይቅርታ የጠየቀችው ድምጻዊት ቪሮኒካ አዳነ በድጋሚ በሚኖር ዝግጅት እንደምትክሳቸውም በመልዕክቷ አስታውቃለች።
ቪሮኒክ በአሁኑ ሰአት የህክምና ክትትል እየተደረገላት እንደሚገኝም በማህበራዊ ትስስር ገጿ በለቀቀችው ምስል ላይ አስታውቃለች።
ቬሮኒካ "ተው"፣ "ኩርፊያ"፣ "ጥፍጥ አለኝ"፣ "አበባዬ" በሚሉና ሌሎች የነጠላ ዜማዎቿ ተወዳጅነትን አትርፋለች።
የሙዚቃ ስራዎቿ በዩቲዩብ በሚሊየኖች በመታየት ቀዳሚ ከሆኑ ኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ውስጥም ትመደባለች።
በቅርብ ጊዜ “እናነይ” የሚል መጠሪያ የሰጠችውን የሙዚቃ ቪዲዮ መልቀቋም የሚታወስ ነው።