ሴቶች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ቢያንስ 800 ቢሊዬን ዶላር ገቢ አጥተዋል ተባለ
ባለፈው ዓመት ብቻ ከ64 ሚሊዬን በላይ ስራዎችን ማጣታቸው ነው ኦክስፋም በሪፖርቱ ያመለከተው
ታጣ የተባለው ገቢ ከ98 ሃገራት ጥቅል ዓመታዊ የምርት መጠን የሚልቅ ነው ተብሏል
የኮሮና ወረርሽኝ በሚሊዬን የሚቆጠሩ የዓለማችንን ሴቶች ለስራ አጥነት እና ገቢ እጦት መዳረጉን የኦክስፋም ኢንተርናሽናል ጥናታዊ ሪፖርት አመለከተ፡፡
ሪፖርቱ በወረርሽኙ ምክንያት ሴቶች ያገኙት ከነበረው ዓመታዊ ገቢ ቢያንስ 800 ቢሊዬን ዶላር ያህል አጥተዋል ብሏል፡፡
ሴቶቹ አጡት የተባለው ገቢ ከ98 ሃገራት ጥቅል ዓመታዊ የምርት መጠን (ጂዲፒ) የሚልቅ ነው እንደ ሲኤንኤን ዘገባ፡፡
ኦክስፋም ወረርሽኙ ሴቶችን ለከፉ ችግሮች ዳርጓል ብሏል፡፡
በተለይም ዝቅተኛ ክፍያን በሚያስገኙ፣ እምብዛም የስራ ደህንነታቸው ባልተጠበቁ የስራ ዘርፎች የተሰማሩቱ የበለጠ ለገቢ እጦት መዳረጋቸውን ነው የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር የተናገሩት፡፡
መንግስታት ችግሩን ከማስተካከል ይልቅ ሴቶች የሚሰሩትን ስራ እስከዚህም የማያስፈልግ አድርገው መመልከታቸውንም ነው ጋብሬላ ቡቸር የሚናገሩት፡፡
ይህ ደግሞ በመደበኛነት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ሴቶች ብቻ ባጡት በትንሹ 800 ቢሊዬን ዶላር ገደማ ገንዘብ የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ታጣ የተባለው ገንዘብ በኢ-መደበኛ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው የራሳቸውን ገቢ ያመነጩ የነበሩ በሚሊዬን የሚቆጠሩ ሴቶችን የሚያካትት አይደለም፡፡
ባለፈው ዓመት ብቻ ከ64 ሚሊዬን በላይ ስራዎችን ማጣታቸውም ተነግሯል፡፡
ሴቶች በወረርሽኙ ክፉኛ በተጎዱ የአገልግሎትን መሰል የስራ ዘርፎች በብዛት ተሰማርተው የሚገኙ መሆኑ ከወንዶች በበለጠ ለስራ አጥነት ተጋላጭ አድርጓቸዋል፡፡
“ከወረርሽኙ በፊትም የእኩልነት ችግሮች ነበሩ፤ አሁን ደግሞ ይበልጡኑ ተባብሰዋል”ም ነው ዋና ዳይሬክተሯ ያሉት፡፡