ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከቤተሰቦቻቸው ቢዝነስ ጋር በተያያዘ ምርመራ ሊደረግባቸው ነው
ሪፐብሊካኖች የፊታችን ጥር ስራ ሲጀምሩ በጆ ባይደን ቤተሰብ ላይ ምርመራ እንደሚከፍቱ ተናግረዋል
የአሜሪካ ምክር ቤት ምርጫ በሪፐብሊካኖች ብልጫ መጠናቀቁ ይታወሳል
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከቤተሰቦቻቸው ቢዝነስ ጋር በተያያዘ ምርመራ ሊደረግባቸው ነው።
በየሁሉት ዓመቱ የሚካሄደው የአሜሪካ ምክር ቤት ምርጫ ባሳለፍነው ሳምንት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በዚህ ምርጫ ላይ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዲሞክራት ፓርቲ በተቀናቃኛቸው ሪፐብሊካኖች ፓርቲ አብላጫ ተወስዶባቸዋል።
አዲስ ተመራጭ የምክር ቤት አባላት የፊታችን ጥር ወር ላይ ስራ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
በምክር ቤቱ አብላጫ ወንበር የተቆጣጠሩት ሪፐብሊካኖች ስራ ሲጀምሩ በፕሬዝዳንት ባይደን እና ቤተሰባቸው ቢዝነስ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የፕሬዝዳንት ባይደን ልጅ የሆኑው ሀንተር ባይደን በአሜሪካ እና ሌሎች የዓለማችን ሀገራት ላይ እያካሄዱት ባለው ንግድ ዙሪያ ምርመራ ማድረግ አቅደዋል።
ምርመራው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቤተሰቦቻቸው እያካሄዱት ባለው ንግድ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እና ፕሬዝዳንትነታቸውን ተጠቅመው የሰሩት ያላግባብ ስራ መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ ዋነኛ ትኩረቱ እንደሚሆን በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ፓርቲያቸው በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እስካሁን ምላሽ ያልሰጡ ሲሆን ሌሎች የአሜሪካ ፖለቲከኞች ግን የዲሞክራቶች ድርጊት የሀገሪቱን አንድነት የሚጎዳ ነው ብለዋል።
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዝዳንት ባይደን ላይ ምርመራ እንዲደረግ ብርቱ ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጿል።
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ የሆነው ሀንተር ባይደን በንግድ ስራ የተሰማሩ ሲሆን በዩክሬን ግዙፍ የቢዝነስ ተቋም እንዳላቸው ይነገራል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቀድሞ ፕሬዝዳንት የሆኑት ጆ ባይደን ድርጊት የአሜሪካን ዲሞክራሲ እየጎዳ መሆኑን ከዚህ በፊት መናገራቸው አይዘነጋም።