የአሜሪካ ዲሞክራሲ በዶናልድ ትራምፕ ምክንያት እየተጎዳ መሆኑን ፕሬዝዳንት ባይደን ተናገሩ
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የ2020 ምርጫ ውጤትን አልቀበልም ማለታቸው ይታወሳል
ባይደን፤ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች አደገኛና በአሜሪካን የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲፈጠር እያደረጉ ነው ብለዋል
የአሜሪካ ዲሞክራሲ በዶናልድ ትራምፕ ምክንያት እየተጎዳ መሆኑን ፕሬዝዳንት ባይደን ተናገሩ።
በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው የአሜሪካ ዋነኛ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት ምርጫ ከቀናት በኋላ የሚካሄድ ሲሆን ከወዲሁ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል።
ፕሬዝዳንት ባይደን የሚፈልጓቸውን ጉዳዮች በቀላሉ ለማስፈጸም የምክር ቤቱን አብላጫ ወንበር ለመያዝ ብርቱ ፉክክር በማድረግ ላይ ሲሆኑ ከተቀናቃኛቸው ሪፐብሊካን ፓርቲ ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ተገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዶናልድ ትራምፕ የባይደንንን በምርጫው ማሸነፍ እንደማይቀበሉ መናገራቸው ይታወሳል።
ዶናልድ ትራምፕ ይህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ተሰርቋል ብለው ከማሰባቸው ባለፈ ለደጋፊዎቻቸው መናገራቸው በወቅቱ በአሜሪካ ሁከት ተከስቶም ነበር።
ይህ የሁለቱ ፖለቲከኞች አለመተማመን በአሁኑ የህግ አውጪ ምክር ቤት ምርጫ ላይ ዋነኛ ስጋት መሆኑን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ዲሞክራሲን እየጎዳ ነው፣ ከሁለት ዓመት በፊት ምርጫው መጭበርበሩን የነገራቸው ደጋፊዎቹ አሁንም ጉዳት እያደረሱ ናቸውም ብለዋል።
ይሄንንም ተከትሎ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች አደገኛ እና በአሜሪካንን የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዳይፈጠር እያደረገ መሆኑንም ፕሬዝዳንት ባይደን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል፣ በፕሬዝዳንትነት የነበረውን ስልጣን ላልተገባ ነገር ተጠቅሟል ሲሉም ከሰዋል።
በ2020 የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በሀገሪቱ ምርጫ ታሪክ አደጋ ያጋጠመው ሆኖ ተመዝግቧል ያሉት ፕሬዝዳንት ባይደን የምርጫው ውጤትም በታሪካችን መጠራጠር የታየበት ነውም ብለዋል።
የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ባለቤት ከሰሞኑ በመኖሪያ ቤታቸው በመዶሻ ጥቃት የደረሰባቸው ሲሆን የጥቃቱ መንስኤ ይሄው የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
አሜሪካዊያን ዲሞክራሲያቸው በሀሰት እና ለትርፍ ተብሎ ወደ ባሰ አደጋ እንዳይገባ የመከላከል ታሪካዊ ሃላፊነት አለባችሁ ያሉት ፕሬዝዳንቱ በምርጫው እንዲወስኑ ጥሪ አቅርበዋል።