በፕሬዝዳንት ባይደን ላይ ስጋትን የደቀነው የአሜሪካ ምክር ቤት ምርጫ ከ2 ሳምንት በኋላ ይካሄዳል
የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ደግሞ በየአራት ዓመቱ ይካሄዳል
በምክር ቤቱ ምርጫ ሪፐብሊካኖች አብላጫ መቀመጫዎችን ካገኙ ፕሬዝዳንት ባይደን ፈተና ይበዛባቸዋል ተብሏል
የአሜሪካ ምክር ቤት ምርጫ ከሁለት ሳምንት በኋላ ይካሄዳል።
የአሜሪካ ዋነኛ የስልጣን ማዕከላት የሚባሉት የኮንግረስ እና ሴኔት ምክር ቤቶች ምርጫ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን የዘንድሮው ምርጫ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
435 መቀመጫ ያሉት የአሜሪካ ምክር ቤት ምርጫ ሪፐብሊካን እና ዲሞክራት ፓርቲዎች አንዱ በአንዱ ላይ ከ30 እስከ 40 መቀመጫዎችን በበላይነት ለመቆጣጠር ፍላጎት አላቸው ተብሏል።
የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፓርቲ የሆነው ዲሞክራት ፓርቲ አሁን ላይ ከ435 መቀመጫዎች 220ዎቹን የተቆጣጠረ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚካሄደው የምክር ቤት ምርጫ አብላጫ ወንበሮች ሊወሰድባቸው እንደሚችል ተሰግቷል።
አሁን ላይ 212 የምክር ቤት መቀመጫዎችን የተቆጣጠረው ሪፐብሊካን የተሰኘው ፓርቲ በዚህ ምርጫ ላይ አብላጫ መቀመጫዎችን ከተቆጣጠረ ለፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፈተና ሊሆንባቸው እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል።
ሪፐብሊካኖች ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚካሄደውን የምክር ቤት ምርጫ አብላጫ መቀመጫዎችን ከተቆጣጠሩ በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ላይ ምርመራ እንዲጀመር እና ከስልጣን እንዲለቁ የሚያደርጉ ስራዎች ሊጀመሩ ይችላሉም ተብሏል።
ይሁንና ዲሞክራተሮች በቀላሉ በሪፐብሊካኖች ብልጫ እንዲወሰድባቸው እንደማያደርጉ የተገለጸ ሲሆን በተለይም ከፍተኛ ፉክክር ሊደርግባቸው በሚችልባቸው እንደ ፔንሲልቫኒያ፣ ጆርጂያ፣ ዊንስኮንሲን እና ኔቫዳ ግዛቶች ላይ ያልተጠበቁ ውጤቶች ሊመዘገቡ እንደሚችሉ ተገልጿል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ያስከተላቸው ጉዳቶች፣ የጽንስ ማቋረጥ ህግ፣ የኑሮ ውድነት፣ የጦር መሳሪያ አዋጅ፣ የስደተኞች አዋጅ፣ የድንበር ቁጥጥር ፖሊሲ እና ሌሎች ጉዳዮች መራጮችን ያልተጠበቀ ውሳኔ እንዲወስኑ ሊያደርጋቸው ይችላልም ተብሏል።