የትራምፕ ፓርቲ ግሪንላንድን ለመግዛት ያስችላል የተባለ ረቂቅ ህግ አቀረበ
ረቂቅ ህጉ የሚጸድቅ ከሆነ ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን በፈጸሙት እለት ከዴንማርክ ጋር ወደ ድርድር መግባት ይችላሉ
ትራምፕ ከግሪንላንድ በተጨማሪ ፓናማ ቦይን የመቆጣጠር እና ካናዳን 51 የአሜሪካ ግዛት የማድረግ ሀሳብ እንዳላቸውም ሲናገሩ ተደምጠዋል
የትራምፕ ፓርቲ ግሪንላንድን ለመግዛት ያስችላል የተባለ ረቂቅ ህግ አቀረበ።
የተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት የተወካዮች ምክር ቤት ረፐብሊካን አጋሮች ግሪንላንድን ለመግዛት ያስችላል የተባለው ረቂቅ ወደ ስራ እንዲገባ ድጋፍ እያሰባሰቡ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ረቂቅ ህጉ "ሜክ ግሪንላንድ ግሬት አጌን አክት" ወይም 'ግሪንላንድን በድጋሚ ታላቅ እናድርጋት ውል' የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ረቂቅ ህጉን እየመሩ ያሉት የሪፐብሊካን የአሜሪካ ቢሮዎች ተወካይ አንዲይ ኦግሊስ እና ዲያና ሀርሽባርገር ተናግረዋል። የረቂቅ ህጉ ኮፒ ቀደም ሲል በፎክስ ኒውስ ዲጂታል ሪፖርት መደረጉን እና እስከ ሰኞ ድረስ ከ10 በላይ ቦታዎች መውጣቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ትራምፕ ግሪንላንድ የአሜሪካ ግዛት አካል ሆኖ እንድትጠቃለል እንደሚፈልጉ መግለጻቸው እና ይህን ለማሳካት ወታደራዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ አማራጮችን ከመጠቀም ወደ ኋሃ እንደማይሉ አመላክተዋል። ከሁለት ወራት በፊት በተካሄደው ምርጫ ሪፐብሊካኖች በተወካዮች ምክር ቤት እና በሰኔት በጠባብ ልዩነት የበላይነት ይዘዋል።
ረቂቅ ህጉ የሚጸድቅ ከሆነ ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን በፈጸሙት እለት ከዴንማርክ ጋር ወደ ድርድር ይገባሉ ማለት ነው።
"ኮንግረሱ ፕሬዝደንት ትራምፕ ግራንላንድን ለአሜሪካ አካል ለማድረግ ከዴንማርክ ጋር የሚያደርጉትን ድርድር ከጥር 20፣2025 ጀምሮ እንዲጀምሩ ፈቅዷል" የሚል አንቀጽ በረቂቅ ህጉ ውስጥ መካተቱን ዘገባው ጠቅሷል።
ረቂቅ ህጉ አክሎም "በግሪንላንድ ግዥ ላይ ከዴንማርክ ጋር ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ከአምስት የስራ ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ፕሬዝደንቱ ስምምነቱን ለሚመለከተው የኮግሬሽናል ኮሚቴ ማስተላለፍ አለባቸው" ይላል።
ግሪንላንድ ቀደም ሲል እንደቅኝ ግዛትና አሁን ደግሞ እንደ ከፊል ራስ ገዝ አስተዳደር ለ 600 አመታት በዴንማርክ ቁጥጥር ስር ነች። ሀገሪቱ በዴንማርክ ህገመንግስት የምትመራ ሲሆን ሊኖር የሚችል ማንኛውንም ለውጥ የህገመንግስት ማሻሻያ ይሻል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ሙቴ እግዴ ደሴቷ ለሽያጭ እንደማትቀርብ እና አጣፋንታዋ የሚወሰነው በህዝብ እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጸዋል።
ትራምፕ ከግሪንላንድ በተጨማሪ ፓናማ ቦይን የመቆጣጠር እና ካናዳን 51 የአሜሪካ ግዛት የማድረግ ሀሳብ እንዳላቸውም ሲናገሩ ተደምጠዋል።