የምግብ ዋጋ መናር ዓለምን አሳስቧል
በኢትዮጵያ ባሳለፍነው ግንቦት ወር የምግብ የዋጋ ግሽበት የ22.6 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የስታቲስቲክስ መረጃዎች አመልክተዋል
የምግብ ዋጋ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ከነበረው የ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ፋኦ አስታውቋል
የምግብ ዋጋ ከ10 ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ማሻቀቡ እንዳሳሰበው የዓለም የምግብና የግብርና ድርጅት (ፋኦ) አስታወቀ፡፡
ፋኦ የዋጋ ንረቱ ምናልባትም ወትሮውኑ ሰላም ላጡ ሃገራት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆን መስጋቱን አስታውቋል፡፡
እንደ ድርጅቱ ከሆነ የምግብ ዋጋ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ከነበረው የ40 በመቶ ገደማ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ይህ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2011 ወዲህ ያልታየ አዲስ ነገር ነው፡፡
በ2007/8 አካባቢ አጋጥሞ የነበረው የምግብ ዋጋ ንረት ምክንያት በአንዳንድ ሃገራት ግጭቶች ተቀስቅሰው ነበር፡፡
ንረቱ በከፋበት በ2011 አካባቢ የአረብ የጸደይ አብዮት ተቀጣጥሎ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ የደቀቀው የዓለም ምጣኔ ሃብት አሁን አሁን እየተነቃቃ ነው፡፡ ሃገራት ከባለፈው ዓመት የተሻለ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንደሚያስመዘግቡም ይጠበቃል፡፡
ሆኖም እድገቱ እንደየሃገራቱ ለየቅል ነው፡፡ በተለይ አሁንም ከወረርሽኙ በወጉ ለማገገም ያልቻሉ አዳጊ ሃገራት ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የተቀዛቀዘ እና በከፍተኛ የገቢ እጦት የተጎዳ ነው፡፡
ይህ ከድርቅና ሌሎች ምክንያቶች ጋር ተደማምሮ የምግብ ዋጋ እንዲንር ምክንያት ሆኗል፡፡
አፍሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ እና የተለያዩ የእስያ ሃገራት የገፈቱ ቀማሾች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ተመሳሳይ ሁኔታዎች መታየታቸውና ኑሮ መወደዱ ይነገራል፡፡ የዛሬ ዓመት የነበረው የምግብ ሸቀጦች የመግዣ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯልም ይባላል፡፡
በግንቦት ወር 2013 ዓ/ም አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት የ19.9 በመቶ ጭማሪ ባሳየባት ኢትዮጵያ የምግብ የዋጋ ግሽበት የ22.6 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን አል ዐይን አማርኛ ከኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ያገኘው አሃዛዊ መረጃ ያመለክታል፡፡