መንገዶቹ የተዘጉት በለውጡ የተገደሉ ሰዎች መታሰቢያ ስነ ስርዓት ይካሄዳል መባሉን ተከትሎ ነው
የሱዳን ጦር ወደ ሀገሪቱ መከላከያ መስሪያ ቤት የሚወስዱ ሁሉም መንገዶች ዝግ መደረጋቸውን አስታወቀ፡፡
የሱዳን ጦር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት መንገዶቹ እንዲዘጉ የተደረገው ከሁለት ዓመት በፊት በነበረ ተቃውሞ የተገደሉ ንጹሃንን ለማሰብ በሚደረገው ሰልፍ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በሱዳን መዲና ካርቱም የቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ኦመር ሃሰን አልበሽር ከሥልጣን ከተነሱ በኋላ በነበረ ተቃውሞ የተገደሉ ሱዳናውያንን ለማሰብ ነው ተብሏል፡፡
በወቅቱ አልበሽር ከስልጣን ተነስተው በእነ ሌ/ጄ አብዱልፋታህ አልቡርሃን የሚመራው ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ወደ ኃላፊነት ቢመጣም ሱዳናውያኑ ግን፤ በእነ አል ቡርሃን የሚመራውን የሽግግር መንግስትንም ተቃውመዋቸው ነበር፡፡
በወቅቱ በነበረው ተቃውሞም በርካታ ንጹሃን መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ እነዚህን ለማሰብ ዛሬ በካርቱም ሰልፍ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ተቃውሞ በማሰማት ላይ ሳሉ በጸጥታ ኃይሎች የተገደሉ ዜጎችን ለማሰብ ዛሬ በሚደረግ ዝግጅት ላይ የጸጥታ ችግር እንዳይፈጠር በመፍራት ነው ወደ ሀገሪቱ መከላከያ ዋና መስሪያ ቤት የሚያመሩ ሁሉም መንገዶች የተዘጉት ተብሏል።
በመሆኑም የካርቱም ነዋሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙም ጦሩ ያዘዘ ሲሆን መንገዶቹ ዝግ የሚሆኑት ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ (ዶ/ር) በፈረንጆቹ ሰኔ 3 ቀን 2019 የነበረው ሁኔታ በሁሉም ሱዳናውያን ልብ ውስጥ ነው ብለዋል፡፡
በወቅቱ መስዋዕት ለከፈሉ ዜጎች ክብር ሊሰጥ እንደሚገባም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡