የሀገሪቱ ስልጣን በተግባር በወታደራዊው ክንፍ ብቻ እንደሚገኝ የገለጹት ወ/ሮ አይሻ የስራ መልቀቅያ ደብዳቤ አስገብተዋል
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት አባሏ አይሻ ሙሳ መንግስታቸውን “የዘፈቀደ” ነው በማለት ተችተዋል፡፡ ወ/ሮ አይሻ ሙሳ የስራ መልቀቅያም አስገብተዋል፡፡
የሉዓላዊው ምክር ቤት አባሏ ወ/ሮ አይሻ የሽግግር መንግስቱን በመተቸት መግለጫ ሲሰጡ በእንባ ታጅበው ነበር፡፡
ምክር ቤቱ “ሀሳቦች ችላ የሚባሉበት፣ ሲቪሎች በውሳኔ ሰጪነት ላይ የማይሳተፉበት፣ የህዝብን ችግር መቀነስ የማይችል” ነው በማለት ምሬታቸው ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ ከመከላከያ እና ከሲቪሉ ማህበረሰብ የተውጣጣው ውህድ የሽግግር መንግስት የሱዳንን ህዝብ ችግር መፍታት የማይችል እንደሆነ እና የሀገሪቱን የደህንነት ስጋት እያባባሰ መምጣቱን እንዲሁም ወታደራዊ ኃይሎችን መቆጣጠር እና አደብ ማስገዛት አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የሚገኙበት ሲቪሉ የሽግግር ምክር ቤቱ አካል ፣ ከአባልነት ባለፈ በውሳኔ ሰጪነት ምንም ሚና እንደሌለው እና ወታደራዊው ክንፍ ከሕገ መንግስቱ በላይ ስልጣን እንደሚጠቀምም ነው የገለጹት፡፡
አሁን ያለው “የሽግግር መንግስት አካል መሆን በቃኝ” በማለት ‘ረመዳን 30’ ላይ የመልቀቅያ ጥያቄ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ወ/ሮ አይሻ ፣ መንግሥት በሴቶች ላይ የሚያሳየው የማግለል ድርጊትም ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡ ለዚህም የሱዳንን ሴቶች ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
ችግሮች እንዲቀረፉ ካስፈለገ “የሽግግር አጋሮች ምክር ቤት መፍረስ ፣ የፀጥታ አገልግሎቶች እንደገና መዋቀር እንዲሁም የሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትነት ወደ ሲቪል አካል መዛወር አለበት” ነው ያሉት ወ/ሮ አይሻ፡፡
ሱዳንን ለ30 ዓመታት የመሩት የቀድሞው ፕሬዝደንት ኦማር አል በሽር እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 2019 በመፈንቅለ መንግስት መነሳታቸውን ተከትሎ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የተመሰረተው ሉዓላዊ የሽግግር ም/ቤት የሀገሪቱን ችግር መቅረፍ እንዳልቻለ ይነገራል፡፡ በተለይ በሀገሪቱ ያለው የኢኮኖሚ ቀውስ መሻሻል ማሳየት አልቻለም፡፡ በሱዳን ጉዳይ በፓሪስ ከተካሔደው ጉባዔ በኋላ ፣ ምንም እንኳን ሀገሪቱ የተለያዩ ድጋፎች እንደሚደረጉላት ቃል ቢገባም የሀገሪቱ የገንዘብ አቅም አሁንም በከፍተኛ ደረጃ በመውረድ ላይ ይገኛል፡፡