በአጠቃላይ አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ ሮቦቶች 70 በመቶዎቹ የሚገኙት በእስያ ነው
ዘመናዊው አለም የቴክኖሎጂን መራቀቅ ተከትሎ ሮቦቶችን ከአስተናጋጅነት እስከ ፋብሪካ ሰራተኛነት ማሰማራት እየተለመደ መጥቷል።
በእርግጥ ሮቦቶችን በፋብሪካዎች ውስጥ መጠቀም ከተጀመረ ትንሽ የቆየ ቢሆንም የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም እያደገ መምጣት ሮቦቶች የሚገቡበትን የስራ ዘርፍ እያበዛው ስለመሆኑ ተነግሯል፡፡
ይህን ተከትሎም በአሁኑ ወቅት ሮቦቶች በፋብሪካዎች፣ በህክምና፣ በመስተንግዶ፣ በመኖርያ ቤት ውስጥ በኮንስትራክሽን ፣ በውትድርና እና በሌሎችም የስራ ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡
ሮቦቶች ክፍያ አለመጠየቃቸው፣ እረፍት እና ሀመም በሚል ከስራ አለመቅረታቸው እንዲሁም ከሰው ልጅ ጋር ሲነጻጸሩ ያላቸው ምርታማነት ከፍተኛ መሆን በሰፊው ተመራጭ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሮቦቶች በአለም አቀፍ ደረጃ በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን በ2023 በስራ ላይ የተሰማሩ ሮቦቶች ከ2022ቱ በ10 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የኢንተርናሽናናል ፌደሬሽን ኦፍ ሮቦቲክስ መረጃ ያሳያል፡፡
በአጠቃላይ አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ ሮቦቶች መካከል 70 በመቶ በእስያ፣ 17 በመቶ በአውሮፓ እና 10 በመቶው ደግሞ በአሜሪካ ውስጥ ይገኛሉ።
በርካታ ሮቦቶችን በስራ ላይ በማሰማራት ደቡብ ኮርያ በአለም ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን ከ10 ሺህ ሰራተኞች መካከል 1012ቱ ሮቦቶች ናቸው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው በቴክኖሎጂ እድገት ስማቸው ከሚጠሩ የአለም ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሲንጋፖር ከ10 ሺህ ሰራተኞች 730 ሮቦቶችን በስራ ላይ አሰማርታለች፡፡
ጀርመን ፣ ጃፓን እና ቻይና ከ3ኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ አሜሪካ 10ኛ ላይ ተቀምጣለች።