በጸና የታመሙ ተማሪዎችን ተክቶ ክፍል ውስጥ የሚገባው ሮቦት
ሮቦቱ በህመም ምክንያት ከትምህርት ቤት ለሚቀሩ ተማሪዎች ክፍል ውስጥ በመገኝት ትምህርት እንዳያመልጣቸው ያግዛል ተብሏል
በአሁኑ ወቅት በ17 የአውሮፓ ሀገራት ሮቦቶቹ በሰፊው ጥቅም መስጠት ጀምረዋል
ህጻናት በህመም ምክንያት ከትምህርት ሲቀሩ ከህመሙ ባሻጋር ከክፍል ጓደኞቻቸው መለየታቸው እና ከትምህርታቸው መራቃቸው እንደሚጎዳቸው ይነገራል፡፡
በጽኑ የታመሙ ተማሪዎች መች ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንደሚመለሱ ያለማወቃቸው በአእምሯቸው ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ የማገገሚያ ጊዚያቸውን እንደሚያረዝመው የስነልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ይህን ችግር ይቀርፋል የተባለ የቴክኖሎጂ ውጤት የኖርዌይ ኩባንያ አስተዋውቋል፡፡
ኤቪ 1 የተባለው ሮቦት በህመም ምክንያት ከትምህርት በቀረው ተማሪ ምትክ ክፍል ውስጥ በመገኝት በተገጠሙለት የካሜራ እና ማዳመጫ መሳርያዎች ተማሪው በክፍል ውስጥ የሚሆነውን በሙሉ እንዲከታተል የሚያስችል ናቸው፡፡
360 ዲግሪ አቅጣጫ የሚሽከረከረው ሮቦት የትምህርት ሂደቱን ቀጥታ ከመከታተል ባለፈ ተማሪው ከመምህራን ጋር ለመወያየት ፣ ጥቄዎችን ለመመለስ ፣ እጅ ማውጣት እና ከጎደኞቹ ጋር እንዲነጋገር ያገዛል ተብሏል፡፡
በህክምና መስጫ ተቋማት አልያም በቤቱ ውስጥ የሚገኝው ህመምተኛ ተማሪ በስልኩ ላይ በሚጫን ልዩ መተግበርያ ሮቦቱን በመቆጣጠር በመማርያ ክፍል ውስጥ የሚከናወነውን ሁሉ በግልጽ ሁኔታ መከታተል ይችላል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከ3000 በላይ ኤቪ 1 ሮቦቶች ጀርመን እና ብሪታንያን ጨምሮ በ17 የአውሮፓ ሀገራት በስራ ላይ ሲገኙ አንድ ሺህ ተጨማሪ ሮቦቶች በምርት ላይ እንደሚገኝ የሮቦቶቹ አምራች የኖርዌዩ ኩባንያ አስታውቋል፡፡
በብሪታንያ ሮቦቱን በኪራይ ለአንድ ወር ለመጠቀም 200 ዶላር የሚያስከፍል ሲሆን ለግዢ ደግሞ 4960 ዶላር ዋጋ ተቆርጦለታል፡፡
በ2023/24 አመት በብሪታንያ ብቻ 19 በመቶ ተማሪዎች በጸና ህመም ምክንያት ከትምህርታቸው መራቃቸው ሲነገር ይህም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽ ወቅት ከነበረው የ7.8 በመቶ ብልጫ እንዳለው ሲኤንኤን አስነብቧል፡፡
ደካማ የዋይፋይ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ባለባቸው አካባቢዎች የሚጋጥመውን የስርጭት መቆራረጥ ለማስቀረት ሮቦቶቹ እየሰጡት ከሚገኝው አገልግሎት አንጻር ትምህርት ቤቶች የኢንተርኔት መሰረተ ልማቶችን ለማሻሻል እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡