በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ የኢራኑን ፔርሴፖሊስ የገጠመው አል ናስር ያለግብ ተለያይቷል
የሳኡዲው ክለብ አል ናስር አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ያገኘውን እድል ሁሉ ተጠቅሞ ጎል ሲያስቆጥር ነው የሚታወቀው።
ትናንት ምሽት ግን የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ተገቢ አይደለም በሚል ዳኛውን አሳምኖ እንዲሻር አድርጓል።
አል ናስር ከኢራኑ ፐርሴፖሊስ ጋር በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣሪያ ሲጫወት ነው ያልተለመደው ክስተት የታየው።
ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ በሮናልዶ ላይ ጥፋት ተሰርቷል ያሉት ቻይናዊው የመሃል ዳኛ ማ ኒንግ የፍጹም ቅጣት ምት ሰጥተዋል።
የ38 አመቱ ፖርቹጋላዊ ግን ዳኛውን ጥፋቱ ፍጹም ቅጣት ምት አያሰጥም በሚል ያነጋግራቸዋል።
የሮናልዶን የፍጹም ቅጣት ምት አይገባኝም ምላሽ የያዙት ኒንግም በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቫር) ተጠቅመው ውሳኔያቸውን ቀልብሰዋል።
የሮናልዶ ሃቀኝነት የኢራኑን ፐርሴፖሊስ ከሽንፈት ታድጎታል፤ ጨዋታው ያለግብ ተጠናቆ አንድ ነጥብ ይዞ ወደ ቴህራን ተመልሷል።
አል ናስር በእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ አስቀድሞ ወደ ጥሎ ማለፉን አረጋግጧል።
የሮናልዶ ክለብ ምድቡን በ13 ነጥብ እየመራ ነው ማለፉን ያረጋገጠው።
የትናንቱ የሪያድ ተጋጣሚው ፐርሴፖሊስ በአምስት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።