ሮናልዶ የ2023 “የማራዶና ሽልማት”ን አሸነፈ
ፖርቹጋላዊው ተጫዋች በዱባይ ስፖርት ምክርቤት ድጋፍ የሚዘጋጀውን ሽልማት ያሸነፈው በአመቱ በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር ነው
የሳኡዲው አል ናስር ክለብ ተጫዋች በ2023 54 ጎሎችን አስቆጥሯል
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የ2023 ”ማራዶና ሽልማት”ን አሸነፈ።
ሮናልዶ የፒኤስጂውን ኪሊያን ምባፔ፣ የባየርሙኒኩን ሃሪ ኬን እና የማንቸስተር ሲቲውን ኧርሊንግ ሃላንድ በመብለጥ ነው የአመቱ ምርጥ ጎል አስቆጣሪ ተብሎ የተመረጠው።
14ኛው የዱባይ ግሎብ ሶከር አዋርድ ከሁለት ሳምንት በኋላ በዱባይ ሲካሄድም ሮናልዶ ሽልማቱን ይወስዳል ተብሏል።
የ”ማራዶና አዋርድ” በዱባይ ስፖርት ምክርቤት ድጋፍ በየአመቱ ድንቅ ብቃት ላሳዩ ተጫዋቾች የሚበረከት ሽልማት ነው።
የሳኡዲው አል ናስር ክለብ ተጫዋቹ ሮናልዶ በ2023 59 ጨዋታዎችን በማድረግ 54 ጎሎችን አስቆጥሯል።
በ2017 ለስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ሲጫወት ካስቆጠራቸው ጎሎች በአንድ የሚልቅ ጎል ለአል ናስር ያስቆጠረው ሮናልዶ በሳኡዲ ስኬታማ ቆይታ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የሮናልዶ ተፎካካሪዎች ምባፔ (በ53 ጨዋታዎች 52 ጎል)፣ ሃሪ ኬን (በ57 ጨዋታዎች 52 ጎል) እና ሃላንድ (በ60 ጨዋታዎች 50 ጎል) በተጠናቀቀው 2023 ማስቆጠር ችለዋል።
በጥር ወር 2023 ከማንቸተር ዩናይትድ ወደ ሳኡዲው አል ናስር የተዘዋወረው ፖርቹጋላዊ አጥቂ የሳኡዲ ፕሮ ሊግ ድምቀት ሆኗል።
የ38 አመቱ ተጫዋች ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሲያመራ በአለማቀፍ መድረክ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ ለመፎካከር ይከብደዋል ያሉት ብዙዎች ቢሆኑም ሮናልዶ ለአል ናስር እስካሁን በተሰለፈባቸው 50 ጨዋታዎች 44 ጎሎችን በማስቆጠር አይበገሬነቱን አሳይቷል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በክለብና በአለማቀፍ ውድድሮች 873 ጎሎችን በማስቆጠር የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪ ክብርን እንደያዘ ነው።