በሞሮኮው ርዕደ መሬት አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ2ሺ አለፈ
በአደጋው ታሪካዊቷ ማራካሽ ከተማ መጠነ ሰፊ የሆነ ውድመት አጋጥሟታል
ርዕደ መሬቱ በሬክተር ስኬል ሲለካ 6. 8 መሆኑን እና መነሻውም ከማራካሽ ደቡብ ምዕራብ 72 ርቀት እንደነበር የአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ገልጿል
በሞሮኮ በተከሰተው የርዕደ መሬት አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ2000 ማለፉን እና ሰዎችም ውጭ እያደሩ መሆኑ ተገልጿል።
በሀገሪቱ በስድስት አስርት አመታት ውስጥ በተከሰተው ከባድ እና አሰካሁን ለ2ሺ ሰዎች ሞት ምክንያት ከሆነው ርዕደ መሬት የተረፉት ሰዎች በአትላስ ተራሮች ከቤት ውጭ ለማደር ተገደዋል።
ነዋሪዎች እስካሁን ድረስ በጭቃ፣ በእንጨት እና በድንጋይ ከተሰሩ ቤቶች ፍርስራሾች ውስጥ የተረፉ ሰዎችን እየፈለጉ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
በአደጋው ታሪካዊቷ ማራካሽ ከተማ መጠነ ሰፊ የሆነ ውድመት አጋጥሟታል።
የሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው በአደጋው 2012 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 2059 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል ብሏል።
ርዕደ መሬቱ በሬክተር ስኬል ሲለካ 6. 8 መሆኑን እና መነሻውም ከማራካሽ ደቡብ ምዕራብ 72 ርቀት እንደነበር የአሜሪካው ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ገልጿል።
የርዕደ መሬት አደጋው በተነሳበት አሚዝሚዝ መንደር አካባቢ ነዋሪዎች ፍርስራሾችን በእጃቸው ሲያነሱ ተስተውለዋል።
ነዋሪዎቹ በአደጋው ህይወታቸው ያለፉትን በመቅበር እና በፍርስራሾች ውሰጥ ያሉትን ነፍስ ለማዳን በመጣደፍ ላይ ናቸው።