“እኔ ክብረወሰኖችን አላሳድድም ክብረወሰኖች ራሳቸው ያሳድዱኛል”- ሮናልዶ
ሮናልዶ ዛሬ ለሀገሩ 200ኛ ጨዋታውን በመጫወት አዲስ ታሪክ እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል
የ5 ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው ሮናልዶ ለፖርቹጋል 122 ጎሎችን በማስቆጠር የክብረወሰን ባለቤት ነው
በእግር ኳሱ ዓለም የተለያዩ ክብረወሰኖች ባለቤት የሆነው ፖርቹጋላዊው ክርስቲያኖ ሮናልዶ፤ “እኔ ክብረወሰኖችን አላሳድድም ክብረወሰኖች ራሳቸው ያሳድዱኛል እንጂ” ማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
በዛሬው እለት ምሽት ለሀገሩ ፖርቹጋል 200ኛ ጨዋታውን በመጫወት አዲስ ታሪክ እንደሚያስመዘግብ የሚጠበቀው ሮናልዶ ከጨዋታው በፊት በሰጠው አስተያየት ነው “ክብረወሰኖች ያሳድዱኛል” ያለው።
ክርስቲያ ሮናልዶ በዛሬው እለት የሚካሄደው የአውሮፓ ሀገራት ዋንጫ የማጣያ ወድድር ላይ ለሀገሩ ፖርቹጋል እንደሚሰለፍ ተነግሯል።
- “እግር ኳስን ካቆምኩ በኋላ ሳዑዲ ውስጥ የራሴ የእግር ኳስ ክለብ ይኖረኛል”- ክርስቲያኖ ሮናልዶ
- ክርስቲያኖ ሮናልዶ ሌሎች ተጫዋቾች የሳዑዱ ክለቦችን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቀረበ
ሮናልዶ ከጨዋታው አስቀድሞ በትናንትናው እለት በሰጠው መግለጫ ላይ፤ “በፖርቹጋል ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ያለኝን ስፍራ እንዲሁ በቀላሉ አሳልፌ አልሰጥም፤ ለብሄራዊ ቡድኑ አሁንም ጠቃሚ እንደሆንኩ ይሰማኛል” ብሏል።
“አሁንም በቡድን ውስጥ ያለኝ ዋጋ ከፍ ያለ እንደሆነ ይሰማኛል፤ ይህም ለእኔ ኩራት ነው” ያለው ሮናልዶ፤ “በጣም የምፈልገው ነገር ቢኖር ፖርቱጋልን መርዳቴን መቀጠል ነው” ሲልም ተናግሯል።
ለፖርቹጋል እስካሁን በስሙ 122 ግቦችን በማስቆጠር የሀገሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክብረወሰን ባለቤት የሆነው ሮናልዶ፤ በግሉ የሚያገኛቸው ስኬቶች የህልሙ ፍጻሜ እንዳልሆኑ ጠቁሟል።
በሳዑዲ አረቢያ ለአል ናስር የሚጫወተው የ38 አመቱ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፤ ሀገሩ በአለም አቀፍ መድረክ የበለጠ ስኬት እንድታስመዘግብ በጀርመን ለሚካሄደው የ2024 ኢውሮ ለማብቃት ተስፋ አድርጓል።
ሮናልዶ በዛሬው እለት እንደሚያስመዘግብ በሚጠበው 200ኛ ጨዋታ አዲስ ክብረወሰን ዙሪያ በሰጠው አስተያየትም “እውነት ለመናገር እኔ ክብረወሰኖችን አላሳድድም፤ ክብወሰኖች እኔን ያሳድዱኛል እንጂ ሲል ተናግሯል።
“ቤተሰቤን፣ ጓደኞቼን እና የፖርቹጋል ህዝብን ለማስደሰት አሁንም ቢሆን እግር ኳስ መጫወቴን መቀጠል እፈልጋለሁ” ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።
እስከ ፈረንጆቹ 2025 ድረስ ለሳዑዲ አረቢያው አል ናስር የእግር ኳስ ክለብ የፈረመው ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ስለ ወደፊቱ እቅድ ማውጣት መጀመሩን ማስታወቁ ይታወሳል።
ሮናልዶ ፤ “በእግር ኳስ ዘመኔ የመጨረሻ ላይ ነው፤ ቢበዛ ሁለት ወይ ሶስት ዓመት ቢቀረኝ ነው፤ የእግር ኳስ ክለብ ባለቤት መሆን እፈልጋለሁ” ሲል ተናግሯል።