“እግር ኳስን ካቆምኩ በኋላ ሳዑዲ ውስጥ የራሴ የእግር ኳስ ክለብ ይኖረኛል”- ክርስቲያኖ ሮናልዶ
በርካታ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንዲመጡ በር ከፍቻለሁ፤ ቤንዜማ እንደሚመጣ አውቅ ነበር ብሏል
አል ናስር የሚጫወተው ሮናልዶ የሳዑዲ ሊግ “ከአለማችን ተወዳጅ ሊጎች አንዱ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ” ብሏል
ክርስቲያኖ ሮናልዶ የእግር ኳስ ጨዋታ ካቆመ በኋላ የክለብ ባለቤት ለመሆን እቅድ እንዳለው አስታወቀ።
ሮናልዶ በቀጣዮቹ ሁለት አሊያም ሶስት ዓመታት ውስጥ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የራሱ የእግር ኳስ ክለብ ይኖረኛል ብሎ እንደሚያስብ መናገሩን ኢ.ኤስ.ፒ.ኤን አስነብቧል።
እስከ ፈረንጆቹ 2025 ድረስ ለሳዑዲ አረቢያው አል ናስር የእግር ኳስ ክለብ የፈረመው ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ስለ ወደፊቱ እቅድ ማውጣት መጀመሩን ታውቋል።
በዚህም ሮናልዶ በማድሪድ በተዘጋጀ ኦርሶ 9 የፕላስቲክ ጠርሙስ የውሃ ፋብሪካ ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በተፈራረመበት ወቅት፤ “በእግር ኳስ ዘመኔ የመጨረሻ ላይ ነው፤ ቢበዛ ሁለት ወይ ሶስት ዓመት ቢቀረኝ ነው፤ የእግር ኳስ ክለብ ባለቤት መሆን እፈልጋለሁ” ሲል ተናግሯል።
ለሳዑዲ አረቢያው አል ናስር ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ የፈረመው ክርስቲያኖ ሮናልዶ፤ ፈረንሳያዊው የቀድሞ የሪያል ማድሪድ አጥቂ ካሪም ቤንዜማ በሳዑዲ ፕሮ ሊግ ለመጫወት መወሰኑን አድንቋል።
ካሪም ቤንዜማ ከሪያል ማድሪድ የቀረበለትን የ1 ዓመት የኮንትራት ማራዘሚያ ውድቅ በማድረግ ባሳለፍነው ማክሰሰኞ ምሽት ለሳዑዲው አል ኢትሃድ ክለብ መፈረሙ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ሮናልዶ በሰጠው ስተያየት፤ ወደ ሳኡዲ አረቢያ በማቅናቴ ለበርካቶች በር ከፍቻለሁ፤ ከሪም ቤንዜማ እንደሚመጣ አስቀድሜ አውቅ ነበር፤ በርካቶች ተከትለውት እንደሚመጡም እርግጠኛ ነኝ ሲልም ተናግሯል።
በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሶስት ዓመታት ውስጥ የሳዑዲ አረቢያ ፕሮ ሊግ “ከአለማችን ተወዳጅ ሊጎች አንዱ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ” ሲልም ገልጿል።
የሳዑዲ አረቢያውን አል ሂላልን ይቀላቀላል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ሊዮኔል ሜሲ ትናንት ለአሜሪካው ኢንተር ማያሚ እንደሚጫወት አስታውቋል።
ሆኖም ግን እንደ ሰርጂዮ ራሞስ፣ ጆርዲ አልባ፣ ሰርጂዮ ቡስኬትስ፣ ንጎሎ ካንቴ፣ አንጄል ዲማሪያ፣ ላጎ አስፓስ እና ሮቤርቶ ፍርሚኒሆ ያሉ ድንቅ ተጫዋቾች የሳዑዲ አረቢያ ሊግን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።