ሊቨርፑል በዚህ የዝውውር መስኮት አምስት አማካዮቹን አጥቷል
የሊቨርፑሉ አማካይ ፋቢንሆ የሳኡዲውን አል ኢትሃድ መቀላቀሉ ተነገረ።
የ29 አመቱ ብራዚላዊ በሶስት አመት ኮንትራት ነው ክለቡን የተቀላቀለው።
ፋቢንሆ ከአል ኢትሃድ የ40 ሚሊየን ፓውንድ የዝውውር ጥያቄ ከቀረበለት በኋላ ከቀያዮቹ ጋር ወደ ጀርመን ለልምምድ አላመራም።
ሊቨርፑል በሲንጋፖር ጨዋታዎችን ሲያደርግም ውሉን ለማጠናቀቅ በሚል አልተጓዘም።
በሃምሌ ወር 2018 ከሞናኮ የመርሲሳይዱን ክለብ የተቀላቀለው ፋቢንሆ በአምስት አመት የአንፊልድ ቆይታው 219 ጊዜ ተሰልፎ 11 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ከክለቡ ጋርም የፕሪሚየር ሊግ፣ ሻምፒዮንስ ሊግ፣ ኤፍኤ ካፕ፣ ሊግ ካፕ እና የፊፋ የክለቦች የአለም ዋንጫን አንስቷል።
ብራዚላዊው አማካይ የሳኡዲ ፕሮ ሊግን ከተቀላቀሉ ስመጥር ተጫዋቾች መካከል ተመድቧል።
በአዲሱ ክለቡ አል ኢትሃድም ከባሎንዶር አሸናፊውና የቀድሞው የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ካሪም ቤንዜማ እና ከቀድሞው የቼልሲ አማካይ ንጎሎ ካንቴ ጋር ይጣመራል ተብሏል።
ሌላኛው የክለብ አጋሩ የነበረው ጆርዳን ሄንደርሰንም ወደ ሳኡዲ በማቅናት ስቴቨን ጀራርድ የሚያሰለጥነውን አል ኢቲፋቅ እንደሚቀላቀል ተገልጿል።
ቀያዮቹ በዚህ የክረምት ዝውውር መስኮት አምስት አማካዮቹን አጥቷል።
ጀምስ ሚልነር፣ አሌክስ ኦክስሌድ ቻምበርሊን እና ናቢ ኬይታም ኮንትራታቸው ይጠናቀቃል።