ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መከሩ
ሄሜቲ “የሀገራችን መጻኢ የተሻለ ለማድረግ ከአሜሪካ ጋር በትብብር እንሰራለን” ብለዋል
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አልቡርሃን ጋር መወያየታቸውም ተገልጿል
የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ሃይል መሪው ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ከአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በስልክ መወያየታቸውን አስታወቁ።
ሄሜቲ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ከብሊንከን ጋር “በወሳኝ ጉዳዮች” ላይ መምከራቸውን ጠቁመዋል።
“በቀጣይ ተጨማሪ ንግግሮች (ከብሊንከን ጋር) ይኖረናል፤ የሱዳንን መጻኢ የተሻለ ለማድረግ በትብብር እንሰራለን”ም ነው ያሉት ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ።
በሱዳን ባለፈው ቅዳሜ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ የት እንዳሉ አይታወቅም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ከሱዳን ጦር እና ከሉአላዊ ምክርቤቱ መሪ ጀነራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ጋር መምከራቸውም ተገልጿል።
ብሊንከን ሁለቱም ወገኖች ተኩስ እንዲያቆሙና የንጹሃንን እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን ደህንነት እንዲያረጋግጡ በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ (አርኤሲኤፍ) መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል።
ሁለቱም ወገኖች በየፊናቸው ድል እንደቀናቸው እየገለጹ ሲሆን፥ ምንም አይነት የድርድር ፍላጎት እንዳላሳዩ የመንግስታቱ ድርጅት የሱዳን መልዕክተኛ ተናግረዋል።
በመዲናዋ ካርቱም የኤሌክትሪክ እና ውሃ አቅርቦት የተቋረጠ ሲሆን፥ እስካሁን በውጊያው ህይወታቸውን ያጡ ንጹሃን ቁጥርም 185 መድረሱን ነው መልዕክተኛው ቮከር ፐርትስ የተናገሩት።
በካርቱምና አካባቢው የቀጠለው የአየር ጥቃትና ውጊያ ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎችን ማቁሰሉንም አክለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሱዳን ያለው የሰብአዊ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ አሳስበዋል።
4ኛ ቀኑን የያዘው ግጭት የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ አስቸጋሪ ሁኔታን መፍጠሩን የድርጅቱ የረድኤት ተቋማት እየገለጹ ነው።
የአለም የምግብ ፕሮግራምም ሶስት ሰራተኞቹ መገደላቸውን ተከትሎ በሱዳን በጊዜያዊነት ስራውን ማቋረጡን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።