በዓለም ዋንጫ ድል ሲከበር ወቅት ተጨዋቿን ያለፈቃዷ የሳመው የስፔን እግርኳስ ኃላፊ ስልጣን ሊለቅ ነው
በስፔን በታችኛው ዲቪዤን ለሚገኙ በርካታ ክለቦች የተጫወተው ሩቢያልስ ጨዋታን ያቆመዉ በፈረንጆቹ 2009 ነበር
ፊፋ ተጨዋቿን ያለፈቃዷ ስሟል በተባለው ሩቢያለስ ላይ የስነስርአት ሂደት መክፈቱን ተከትሎ ሩቢያልስ በፈቃዱ ከኃላፊነት ሊለቅ ነው
የስፔን እግር ኳስ ፌደሬሽን ኃላፊ ሊዩስ ሩቢያልስ በአለም ዋንጫ ድል በሚከበርበት ወቅት ጀኒ ሄርሞሶ የተባለችውን ተጨዋች አፍ ያለፈቃዷ ስሟል በሚል ውግዘት ሲነሳበት መቆየቱ ይታወሳል።
ፊፋ ተጨዋቿን ያለፈቃዷ ስሟል በተባለው ሩቢያለስ ላይ የስነስርአት ሂደት መክፈቱን ተከትሎ ሩቢያልስ በፈቃዱ ከኃላፊነት ሊለቅ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሩቢያልስ በሲድኒ በሴቶች የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር እንግሊዝን 1 ለ 0 ላሸነፉት የስፔን ብሔራዊ ቡድን አባላት ሚዳሊያ በሚሸልምበት ወቅት የተጨዋች ሄርሞሶን ከንፈር በመሳሙ ምክንያት ከፍተኛ ቁጣ አስተናግዷል።
የሩቢያለስ ድርጊት ከውጭ እና ከውስጥ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል፤ የመንግስት ባለስልጣናትም ኃላፊነቱን እንዲለቅ ጠይቀዋል።
ጉዳዩ የተባባሰው ፊፉ የስነስርአት ቅጣት ለመጣል በሂደት ላይ መሆኑን እና ሄርሞሶ የሩቢያልስ ተግባር "ያለቅጣት መታለፍ የለበትም" ካለች በኋላ ነው።
ቀደም ሲል ጉዳዩን ሲያጣጥል የነበረው ሩቢያልስ እየተባባሰ ሲመጣ ባለፈው ሰኞ እለት በቪዲዮ ይቅርታ ጠይቆ ነበር። ነገርግን ይቅርታው ቁጣውን ማብረድ አልቻለም።
የፌደሬሽኑ አመራሮች በትናንትናው እለት በማድሪድ ባደረጉት ስብሰባ በሩቢያልስ እጣ ፋንታ እና ማን ይተካው በሚለው ጉዳይ ላይ መምከራቸው ተገልጿል።
እንደሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ፔድሮ ሮቻ ሩቢያልስን ሊተካ ይችላል የሚል ትልቅ ግምት አግኝቷል።
የፌደሬሽኑ ቃል አቀባይ በዚህ ጉዳይ ምላሽ አልሰጠም።
በስፔን በታችኛው ዲቪዤን ለሚገኙ በርካታ ክለቦች የተጫወተው ሩቢያልስ ጨዋታን ያቆመዉ በፈረንጆቹ 2009 ነበር።
ከአመት በኋላ የስፔን እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ፕሬዝደንት መሆን ቻሉ። በፈረንጆቹ 2017 ለስፔን እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት እጩ ሆኖ እስከቀረበበት ድረስ የማህበሩ ፕሬዝደንት ነበር።
በፈረንጆቹ 2018 የፌጀሬሽኑ ፕሬዝደንት ሆኖ ተመረጠ።