ሩሲያ "የሽብር ጥቃት" ሊፈጽሙ ነበር ያለቻቸውን አራት ዜጎቿን በቁጥጥር ስር አዋለች
ተጠርጣሪዎቹ በቤት ውስጥ በሚዘጋጁ ፈንጂዎች በኡራልስ ከተማ ህዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ ጥቃት ሊያደርሱ ነበር ተብሏል
ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ከጀመረች ወዲህ ተደጋጋሚ የሽብር ጥቃት እየተፈጸመባት ይገኛል
የሩሲያው የፌደራል ደህንነት አገልግሎት (ኤፍኤስቢ) የ"ሽብር ጥቃት" ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር ያላቸውን አራት ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
ሁሉም ተጠርጣሪዎች የሩሲያ ዜጎች መሆናቸውንና እድሜያቸውም በ17 እና 18 መካከል እንደሚገኝም ይፋ አድርጓል።
ተጠርጣሪዎቹ በቤት ውስጥጥ ፈንጂዎችን አዘጋጅተው ከሞስኮ በ1 ሺህ 700 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ኡራልስ ከተማ ህዝብ በተሰበሰበበት ስፍራ ጥቃት ሊፈጽሙ ሲዘጋጁ መያዛቸውንም ነው ኤፍኤሲ የጠቆመው።
የስቬርድሎቭስክ ክልልም በተጠርጣሪዎቹ ላይ የወንጀል ክስ መመስረቱ ተመላክቷል።
ከተጠርጣሪዎቹ ውስጥ ሁለቱ በታህሳስ 22 2024 በሩሲያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ተሽከርካሪ ላይ በተቃጣው ጥቃት ተሳትፎ እንዳላቸው የሩሲያ የፌደራል ደህንነት አገልግሎት (ኤፍኤስቢ) አስታውቋል።
የሩሲያው ታስ የዜና ወኪል ተጠርጣሪዎቹ "የኒዮ ናዚ የቴሌግራም ገጾችን እንደሚከተሉ" እና ሞስኮ በሽብር ከፈረጀቻቸው የሽብር ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላቸው መባሉን ዘግቧል።
አንደኛው ተጠርጣሪም "(በቴሌግራም ገጹ) ፖሊሶች ላይ ጥቃት ማድረስ እንደሚያስፈልግ አንብቤያለሁ" ማለቱ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት አራት ሩሲያውያን ሊፈጽሙት የነበረው ጥቃት ከዩክሬን ጋር ግንኙነት እንዳለው ግን እስካሁን አልተገለጸም።
ሩሲያ በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን ጦርነት ከከፈተች ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሽብር ጥቃት ሙከራዎች ተደጋግመዋል።
በመጋቢት 2024 በሞስኮ በሚገኝ የሙዚቃ ድግስ አዳራሽ ላይ የተፈጸመው ጥቃትም አንዱ ማሳያ ነው።
የ145 ሰዎችን ህይወት ቀጥፎ ከ500 በላይ ለቆሰሉበት ጥቃት የአይኤስ የአፍጋኒስታን ክንፍ አይኤስ-ኬ ሃላፊነት መውሰዱ የሚታወስ ነው።
ከ18 ቀናት በፊትም የሩሲያ የኒዩክሌርና ኬሚካል መከላከያ ሃይል አዛዡ ሌተናል ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ ከቤታቸው ሲወጡ የቦምብ ጥቃት ተፈጽሞባቸው ህይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
የዩክሬን የደህንነት ተቋም (ኤስቢዩ) ሌተናል ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ የተገደሉበትን ዘመቻ መምራቱን የገለጸ ሲሆን፥ ሞስኮ ከዚያ ጥቃት በኋላም በባለስልጣናቷ ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን አከሸፍኩ ማለቷ አይዘነጋም።