የሩሲያ ጀነራል የተገደሉት በዩክሬን "ልዩ ዘመቻ" ነው ተባለ
የዩክሬን የደህንነት ተቋም (ኤስቢዩ) ሌተናል ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ የተገደሉበትን ዘመቻ መምራቱም ተገልጿል
ክሬምሊን ግን ምርመራው መቀጠሉን እንጂ ግድያው በኬቭ ስለመፈጸሙ ማረጋገጫ አልሰጠም
የሩሲያ የኒዩክሌርና የኬሚካል መከላከያ ሃይል መሪው ሌተናል ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ የተገደሉት በዩክሬን "ልዩ ዘመቻ" ነው ተባለ።
የዩክሬን የደህንነት ተቋም (ኤስቢዩ) ጀነራሉ የተገደሉበትን ዘመቻ መምራቱንም ሬውተርስ የተቋሙን ምንጮች ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ምንጭቹ ኪሪሎቭ በጦር ወንጀል የሚፈለጉና "ትክክለኛው ኢላማ" መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ክሬምሊን ግን ምርመራው መቀጠሉን እንጂ ግድያው በኬቭ ስለመፈጸሙ ማረጋገጫ አልሰጠም።
በሩሲያ ጦር ስር ያለው የኒዩክሌር፣ ባዮሎጂካል እና ኬሚካል መከላከያ ሀይል መሪው ሌተናል ጀነራል ኢጎር ኪሪሎቭ በኤሌክትሪክ ሞተር ተደብቆ የተጠመደ ቦምብ ፈንድቶ ነው ህይወታቸው ያለፈው።
ቦምቡ የተጠመደው ከክሬምሊን በ7 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አፓርትመንት ላይ መሆኑንም የሩሲያ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል።
በፍንዳታው ስማቸው ያልተጠቀሰ የኪሪሎቭ አጋዥም መገደላቸው የተነገረ ሲሆን፥ የሩሲያ የምርመራ ኮሚቴ ግድያውን መመርመር መጀመሩ ተገልጿል።
የፎረንሲክ ባለሙያዎችም በስፍራው ተገኝተው ምርመራው መቀጠሉና ውጤቱ በአጭር ጊዜ ይፋ እንደሚደረግም ነው የተዘገበው።
ኪሪሎቭ የሚመሩት ሃይል የኒዩክሌር፣ ኬሚካል እና ባዮሎጂካል ጥቃቶች ሲደርሱ ፈጥኖ በመድረስ ዜጎችን ለመታደግ የሚሰራ ነው።
ይሁን እንጂ ከመከላከል ባሻገር በማጥቃቱ ላይም ተሰማርቷል ስትል ዩክሬን ትከሳለች። ሞስኮ ግን ክሱን አትቀበለውም።
የዩክሬን የደህንነት ተቋም (ኤስቢዩ) ዛሬ በቦምብ ህይወታቸውን ያጡትን የሩሲያ ጀነራል የተከለከሉ የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች እንዲተኮሱ አዘዋል በማለት ትናንት በሌሉበት ክስ መስርቶባቸዋል።
ብሪታንያም በጥቅምት ወር 2024 "የክሬምሊን የተዛባ መረጃን የሚያሰራጩ አፈቀላጤ" ናቸው ባለቻቸው ኪሪሎቭ ላይ ማዕቀብ መጣሏ የሚታወስ ነው።